የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የህዝብ እና የሀገር ጥቅምን በማስቀደም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የህዝብ እና የሀገር ጥቅምን በማስቀደም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል
አሶሳ ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የህዝብ እና የሀገር ጥቅምን በማስቀደም ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ ጋዜጠኞች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በአሶሳ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሞላልኝ መለሰ በወቅቱ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም በማጠናከር ረገድ የድርሻውን እየተወጣ ነው።
መገናኛ ብዙሃን ህጋዊነትን ተከትለው ከሰሩ ለአገር ጥቅም ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ በአንጻሩ የመገናኛ ብዙሃን የይዘት አቀራረብ አገር ሊጎዳ እንደሚችልም አስረድተዋል።
በተለይም 'ስፖንሰር ሺፓች' እና መረጃ ሰጪ ምንጮች መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ድብቅ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት ጥረት ሊኖር ስለሚችል ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
ምክር ቤቱም የአሰራር ስነ ምግባር ደንብ አዘጋጅቶ የምክር ቤቱ አባል በሆኑ ማህበራዊና ዲጂታል ሚዲያዎችን ጨምሮ በመገናኛ ብዙሃን እንዲተገበር የሚያደርገው ጥረት እንዳለም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በዘገባቸው ወቅት የህዝብ እና የአገር ጥቅምን በማስቀደም ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
መገናኛ ብዙሃን መፍትሄን መሠረት ያደረጉ ዘገባዎችን በመስራት ለማህበረሰብ ደህንነት ሃላፊነታቸው መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በተለይም መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ለኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው፣ ለህገ መንግስቱ እና ለሌሎችም ህጎች ተገዢ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በዘገባቸው ላይ የህዝብን ምላሽ ማዳመጥ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሌላውን ዘገባ በተወሰነ ደረጃ ቀባብቶ በማሳመር የራሳቸው አስመስለው ማቅረብ እየታየ በመሆኑን ሊስተካከለ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
በስልጠናው በክልሉ የሚገኙ 40 የሚጠጉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን፤ ስልጠናው እስከ ነገ ይቀጥላል።