የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ ከኢንቨስትመንትና ንግድ ተወዳዳሪነት አኳያ

በቁምልኝ አያሌው

ኢትዮጵያ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ መግባቷን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወቃል። 

የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎም ላለፉት ስድስት ዓመታት የተከማቹ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ ሲወስድ ቆይቷል።

የዕዳ ጫና፣ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ አዝጋሚ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ፣ የሀብት ብክነት፣ ዝቅተኛ የዘርፎች ምርታማነት እና የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸሞችም መንግስት የተረከባቸው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚጠይቁ ዕዳዎች እንደሆኑ ተገልጿል።

የተወሰዱ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ እርምጃዎችን ተከትሎም በ2011 ዓ.ም ተግባራዊ የተደረገው የመጀመሪያ ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚው ወደተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሸጋገር አዲስ ተስፋን አምጥተዋል። 

በዚሁ መነሻነትም የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የዕድገት ምንጮችን ለማስፋት፣ የስራ ዕድል ለመፍጠር እና ማነቆዎችን ለመፍታት በተደረገው ጥረት ውጤት ተገኝቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከ2010 እስከ 2015 ዓ.ም ባሉት በጀት ዓመታት በአማካይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት 7 ነጥብ 1 በመቶ በማድረስ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳዩ ካሉ ሀገራት አንዷ ለመሆን በቅታለች።

ከምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን ኢኮኖሚ በመገንባት ከሰሐራ በታች ካሉ አፍሪካ ሀገራት 3ኛውን ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በመሆን ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች።

ቀሪ ስራዎችን በሚገባ በመስራት አገራዊ ግብን ለማሳካትም በአራት ምሰሦዎች የተገነባው 2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ስራ ገብቷል። ምሰሦዎቹም:-

የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትንና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት፣

ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣

የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዐቅምን ማጠናከር እና ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን አቅም ማሳደግ ናቸው።

የፕሮግራሙ ተግባራዊነት በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት በማምጣት የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሐዝ ዝቅ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመገንባት የተጣለውን ትልቅ ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ከሚተገበሩ በርካታ ጉዳዮች መካከል የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤታማነት ማሻሻል የሚል ይገኝበታል። ይህም ከ2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አራት ምሰሶዎች መካከል የሚጠቀስ ነው።  

ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ተወዳዳሪነት 

መንግስት ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ለብዝኃ ኢኮኖሚ ግንባታ በሰጠው ትኩረት በግብርና፣ ኢንዳስትሪ፣ ቱሪዝሪም፣ ማዕድን እና አይሲቲ የልማት ምሰሶዎች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤቶች ተገኝተዋል።

ምቹ ኢንቨስትመንትና ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትን ለመፍጠርም ሰፋፊ እርምጃዎች ተወስደዋል። 

ለአብነትም ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ወደግል በማዞር ምቹ ኢንቨስትመንትና ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትን ለመፍጠር ሲሰራ ቆይቷል።

በኢንቨስትመንት መስክ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መንግስት ባመቻቸላቸው የኢንዳስትሪ ፓርኮች ተሰማርተው በተኪ እና ወጪ ንግድ ምርት ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ። 

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአልሚ ባለሀብቶች የተደረገው የመሰረተ ልማት አቅርቦት እና የአንድ ማዕከል አገልግሎት ድጋፍ የምርት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ አስችሏቸዋል።  

በዚህም በተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም በጀት ዓመት በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 3 ነጥብ 82 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መሳብ እንደተቻለ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል።

የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ተከልለው የቆዩ የወጪ፣ ገቢ፣ ጅምላና ችርቻሮ የንግድ ዘርፎች የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ገበያው ክፍት ተደርጓል።

በዚህም የውጭ ባለሃብቶች በጥሬ ቡና፣ ቅባት እህል፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳ እና ሌጦ፣ የደን ውጤቶች እና የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ላይ መሳተፍ የሚችሉበት ዕድል ተመቻችቷል።

ኢትዮጵያ እያስመዘገበች የምትገኘውን ዕድገት ለማስቀጠል ከ2013 ጀምሮ እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራበት ይገኛል። 

ዕቅዱም በጥራት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማምጣት፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት፣ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የሴቶችና ወጣቶችን ፍትሕዊነት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ የመሪነት ማረጋገጥ ዓላማን ሰንቋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉም ምርታማነትን በማሳደግ በምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል።

የመጀመሪያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ያስመዘገባቸውን ተጨባጭ ስኬቶች በማስቀጠል ቀሪ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠልም ሁለተኛ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ተደርጓል። 

ሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚያስችል ስራ ፈጣሪ ማህበረሰብ መገንባት እንደሚያስችል ታምኖበታል።

የግሉ ዘርፉ ወደ ላቀ የዕድገት ምዕራፍ እንዲሸጋገር የሚያግዝና አሁን የግሉ ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍ ባለሀብቶች በወሳኝ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ ይደርጋል። 

በተጨማሪም ጥራት ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ጠንካራ የወጭ ንግድ ስርአት እንዲኖር መደላድል ይፈጥራል። 

ፈጠራን በማበረታታት ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እንዲኖር በማድረግ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ረገድም ሚናው የጎላ ነው።

በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት  በማስቀጠል ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ሀገራዊ ራዕይን ዕውን ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም