በፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የአትሌቲክስ ውድድር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ):- በፓሪስ እየተካሄደ በቢሚገኘው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የአትሌቲክስ ውድድር ዛሬ ይጀመራል።

የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከተጀመረ ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን ይዟል።

በውድድሩ ከ203 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 500 ገደማ ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ከሀገራት በተጨማሪ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር የሚወዳደሩ ገለልተኛ አትሌቶችና የስደተኞች ኦሊምፒክ ቡድን ተሳታፊ ናቸው።

ኢትዮጵያም በአትሌቲክስና ውሃ ዋና 38 ስፖርተኞችን ታሳትፋለች።

የኦሊምፒክ የአትሌቲክስ መርሐ ግብር ዛሬ እንደሚጀመር የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል።

ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 በሚካሄደው የወንዶች የ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ የፍጻሜ ውድድር አትሌት ምስጋና ዋቁማ ኢትዮጵያን ወክሎ ይሳተፋል።

አትሌት ምስጋና በተርኪዬ አንታሊያ ከተማ ሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው 30ኛው የዓለም አትሌቲክስ የእርምጃ ውድድር የቡድን ሻምፒዮና ላይ በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድር 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግሉን ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።

አትሌቱ የገባበት ጊዜ የኢትዮጵያ የርቀቱ ክብረ ወሰንም ነው።

በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በካሜሮን ዱዋላ በተካሄደው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ2 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር አትሌት ምስጋና የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።

በጋና ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በተከናወነው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች አትሌት ምስጋና በ20 ኪሎ ሜትር የወንዶች እርምጃ ውድድር አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

በሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም በዛምቢያ ንዶላ በተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ የታዳጊና ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ10 ሺህ ሜትር የእርምጃ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ አስገኝቷል።

በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች መክፈቻ ከዋናተኛዋ ሊና አለማየሁ ጋር የኢትዮጵያን ባንዲራ የያዘው አትሌት ምስጋና በውድድሩ ላይ ሲሳተፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

አትሌቱ በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው በሞሪሺየስ ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው 22ኛው የአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነው።

በወቅቱ አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

አትሌት ምስጋና ኢትዮጵያ ብዙም በማትታወቅበት የ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር ስኬታማ የመሆን ሕልም አለው።

አትሌቱ በውድድሩ የሚሳተፈው የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) በሰጠው የዓለም አቀፍ ኮታ አማካኝነት ነው።

በ20 ኪሎ ሜትር የወንዶች የእርምጃ ውድድር ከ26 ሀገራት የተወጣጡ 49 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

ስዊድናዊው ፔርሱስ ካርልስትሮም፣ ስፔናዊው አልቫሮ ማርቲን፣ ብራዚላዊው ካዮ ቦንፊምና ቻይናዊው ጁን ዣንግ ውድድሩን ያሸንፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ይገኙበታል።

በ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የኦሊምፒክ ክብረ ወሰን የተያዘው በቻይናዊው አትሌት ቼን ዲንግ ነው።

አትሌቱ እ.አ.አ በ2012 በለንደን በተካሄደው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች 1 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ በመግባት የሪከርዱ ባለቤት ሆኗል።

ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ20 ላይ የ20 ኪሎ ሜትር ሴቶች የእርምጃ ውድድር ፍጻሜ ይካሄዳል።

የ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአትሌቲክስ መርሐ ግብር እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

ኢትዮጵያ በ1500 ሜትር፣ በ3000 ሜትር መሰናክል፣ በ5000 ሜትር፣ በ10000 ሜትርና በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ትሳተፋለች።

በተጨማሪም በ800 ሜትር በሴቶችና በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር በወንዶች ትካፈላለች።

ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በውሃ ዋና በሴቶች በሊና አለማየሁ ተወክላለች።

ዋናተኛዋ ሊና ሐምሌ 27 እና 28 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው የ50 ሜትር ነጻ ቀዘፋ ውድድር ላይ ትሳተፋለች።

33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም