የአማራ ክልል ምክር ቤት  መደበኛ ጉባኤ ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ

ባህር ዳር፤  ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፡-  የአማራ ክልል ምክር ቤት በርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ የቀረቡ የተለያዩ ሹመቶችን ተቀብሎ በማፅደቅ መደበኛ ጉባኤውን አጠናቀቀ። 

የክልሉ  ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 8ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከሐምሌ 22ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ሲመክር ቆይቷል።

ምክር ቤቱ በቆይታው የክልሉን የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ከመገምገም ባሻገር የተያዘው በጀት ዓመት የማስፈፀሚያ በጀት መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። 

እንዲሁም የስነ ምግባር ጉድለት የተገኘባቸውን አራት ዳኞች ከስራ ማሰናበትን ጨምሮ በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ በመምከር ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።

 

ዛሬ ደግሞ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ  የቀረቡ የተለያዩ ሹመቶችን ተቀብሎ አፅድቋል። 

በዚህም መሰረት፡- 

1ኛ- አቶ ዓለምአንተ አግደው- የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት፣

2ኛ- አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን - የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት እና 

3ኛ-  አቶ መልካሙ ፀጋዬ -የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙ ናቸው።


 

ተሿሚዎቹ በትምህርት ዝግጅትም ሆነ በስራ የካበተ የስራ ልምድ ያላቸው እንደሆኑ ርዕሰ መስተዳድሩ  ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

እንዲሁም ምክር ቤቱ ለክልሉ ምክር ቤት ለሰው ሃብት አስተዳደርና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበራ ፈንታው፤ ለመንግስት ወጪ ቁጥጥር አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደግሞ ወይዘሮ እመቤት ከበደ አድርጎ ሹመታቸውን በማፅደቅ ጉባኤው መረሃ ግብሩን አጠናቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም