አትሌት ምስጋና ዋቁማ በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር 6ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የእርምጃ ውድድር ፍጻሜ ኢትዮጵያን ወክሎ የተወዳደረው አትሌት ምስጋና ዋቁማ 6ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአትሌቲክስ መርሐ ግብር ዛሬ ተጀምሯል። 

ማለዳ ላይ በተደረገው የ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የእርምጃ ፍጻሜ ውድድር ምስጋና ዋቁማ  1 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ በመግባት 6ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

አትሌት ምስጋና በውድድሩ በርቀቱ የኢትዮጵያን ክብረ ወሰንና የራሱን የግል ምርጥ ሰዓት አሻሽሏል። በመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎው አበረታች የሚባል ውጤት አስመዝግቧል።

በውድድሩ ኢኳዶራዊው ብሪያን ዳንኤል ፒንታዶ 1 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።


 

ብራዚላዊው ካዮ ቦንፊም 1 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ ሁለተኛ፣ ስፔናዊው አልቫሮ ማርቲን 1 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ11 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። 

የእርምጃ ውድድሩ በአስቸጋሪ የአየር ፀባይ ምክንያት በ30 ደቂቃ ዘግይቶ መጀመሩን የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል። 

በውድድሩ ላይ ከተሳተፉ 49 አትሌቶች መካከል 46ቱ ውድድራቸውን አጠናቀዋል። የፔሩው ሴዛር አጉስቶ ሮድሪጌዝና የሕንዱ አትሌት አክሽዲፕ ሲንግ ውድድሩን አቋርጠዋል።

የ28 ዓመቱ የሜክሲኮ አትሌት ሆዜ ሉዊስ ከውድድሩ ውጪ እንዲሆን መደረጉን የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል።    

በተያያዘም የ20 ኪሎ ሜትር ሴቶች የእርምጃ ውድድር ፍጻሜ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ከተያዘለት ጊዜ 30 ደቂቃ ዘግይቶ እንደሚጀመር ታውቋል። በዚሁ መሰረት ውድድሩ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ ይከናወናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም