ለናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈጻሚነት ኢትዮጵያ የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ጥረት በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ለናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈጻሚነት የኢትዮጵያ የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ጥረት በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሣዲቅ አደም ገለጹ።

የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እ.አ.አ በ2010 ለፊርማ ክፍት ሆኗል።  እ.አ.አ ከ2013 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ዩጋንዳና ብሩንዲ ስምምነቱን አጽድቀዋል። 

ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ ሐምሌ 8 ቀን 2024 ማዕቀፉን ያፀደቀች ስድስተኛ ሀገር መሆኗን ተከትሎ ሥምምነቱ ወደ ተፈጻሚነት እንዲገባ የሚያስችል ይሆናል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የሕግ ባለሙያው አቶ ሣዲቅ አደም የሁለተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ጽሁፋቸው በናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አማካኝነት የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን መቋቋም ስላለው አንድምታና ጠቀሜታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።

የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትና ተፈጻሚነትን አስመልክቶም ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ሣዲቅ፤ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እ.አ.አ ከ2010 ጀምሮ ለፊርማ ክፍት ቢሆንም ፀድቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለመግባት የ14 ዓመት ጊዜ መውሰዱን ይናገራሉ።

እ.አ.አ በ1929 እና በ1959 የተፈጸሙ የቅኝ ግዛት የውሃ ውሎችን ለማስጠበቅ የተፋሰሱን ሀገራት ጫና ውስጥ በመክተት ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች የስምምነቱን ተፈጻሚነት እንደጎተተው አመልክተዋል። 

ይሁንና ሀገራቱ ጊዜ ያለፈባቸውንና የጋራ ተጠቃሚነትን የማያሰፍኑትን ውሎችን በመተው በውሃ ሀብት አጠቃቀም የጋራ ትብብር የሚፈጥረውን ስምምነት መተግበር አለብን በሚል ባደረጉት ጥረትና ባሳዩት ቁርጠኝነት ማዕቀፉ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ብለዋል። 

የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ትግበራ ደረጃ መሸጋገር የቅኝ ዘመን ውሎችን ዋጋ የሚያሳጣና በውሃ ሀብት አጠቃቀም ላይ ከዚህ በፊት የነበሩ ጊዜያዊ ማዕቀፎች ወደ ቋሚ አሰራር እንደሚያሸጋግር ነው የምክር ቤቱ አባሉ የገለጹት።

በስምምነቱ ተፈጻሚነት ወቅት የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እንደሚቋቋምና ኮሚሽኑ የውሃ ሀብትን በፍትሐዊነትና በሚዛናዊነት የመጠቀም ጉዳይ ላይ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ስምምነቱ “እኔ ብቻ ልጠቀም” በሚል ለረጅም ጊዜ የቆየውን የተሳሳተ እሳቤ በመቀየር በውሃ ሀብት ትብብር ላይ አዲስ የትርክት ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል። 

የትብብር ስምምነቱ ገቢራዊ መሆን ስምምነቱን ያልፈረሙና ያላጸደቁ ሀገራት ወደ ማዕቀፉ እንዲመጡ ከማድረግ አንጻር በጎ ተጽእኖ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

በተጨማሪም ስምምነቱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት በማምጣት የቴክኒክ፣ የገንዘብና የዲፕሎማሲ ድጋፎችን ለማግኘት እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን የፈረመችና ያጸደቀች የመጀመሪያ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ስምምነቱ አሁን ወዳለበት ምዕራፍ እንዲሸጋገር በዲፕሎማሲና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መስክ የተከናወኑ ስራዎች ወሳኝ እንደነበሩም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የማዕቀፉ ተግባራዊነት ረጅም ጊዜ እንዳይወስድና በፍጥነት ተፈጻሚ እንዲሆን የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን እንዳለባት ጠቅሰው ለዚህም ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በትብብር መስራት ይኖርባታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ የዲፕሎማሲ አማራጮችን በመከተል ስምምነቱ ያለውን ፋይዳ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት እንደሚጠበቅባትም ነው የተናገሩት።

የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ጥረት በማድረግ ስምምነቱን ወደ ትግበራ እንዲገባ አበክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸውና የስምምነቱ ዝርዝር ተፈጻሚት ላይ ያሉ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን ማካሄድ እንዳለባቸው ገልጸዋል።  

ስምምነቱን ያልፈረሙና ያላፀደቁ ሀገራትም ፍትሐዊና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍነውን ስምምነት ተቀብለው ለማዕቀፉ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ምሁራንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ለማዕቀፉ ገቢራዊነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አክለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም