የተማሪዎች ምዘገባ በቴክኖሎጂ መታገዙ ጊዜን ከመቆጠብ ባለፈ የተደራጀ መረጃ ለመያዝ አጋዥ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ የተማሪዎች ምዘገባ  በቴክኖሎጂ  መታገዙ ጊዜን ከመቆጠብ ባለፈ የተደራጀ መረጃ ለመያዝ አጋዥ መሆኑን ወላጆችና የትምህርት ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የተማሪዎችን ምዝገባ በኦን ላይን ለማካሄድ የኢ ስኩል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ አድርጎ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በዚህም በመዲናዋ የሚገኙ ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ኦንላይን በመመዝገብ  ላይ ይገኛሉ፡፡

ኢዜአ የተማሪዎች ምዝገባን በኦንላይን እየሰጡ ባሉ ትምህርት ቤቶች ቅኝት በማድረግ ወላጆችና ርዕሳነ  መምህራንን አነጋግሯል ።

ወይዘሮ አልማዝ አስረስ የተባሉ ወላጅ ቀደም ሲል የነበረው የተማሪዎች ምዝገባ ወላጆችን ውጥረት ውስጥ የሚከትና ምልልስ የበዛበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የተማሪዎች ምዝገባ በዘመናዊ አሰራር መደገፉ ጊዜና ገንዘብን ለመቆጠብ ከማገዙ ባለፈ ያጋጥማቸው የነበረውን እንግልት እንዳስቀረላቸው የተናገሩት ወይዘሮ ሰናይት ወንድሙ የተባሉ ወላጅ ናቸው።


 

በቴክኖሎጂ የታገዘው የምዝገባ ሂደት ወላጆች ሰዓታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያደርግ በመሆኑ  በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት አስር አለቃ አዚዝ አደምኑር ናቸው።

የአለም ብርሃን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ይድነቃቸው አሰፋ፤በበኩላቸው ቀደም ሲል የተማሪዎች ምዝገባ ዲጂታል ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የተማሪዎችን መረጃ በተደራጀና  በአግባቡ ለመያዝ በርካታ  ተግዳሮቶች ነበሩብን ብለዋል።


 

የተጀመረው ዘመናዊ አሰራር መረጃዎች ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ እንዲያዙ በማድረግ ለትምህርት ቤቶች ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም መንግስት ለተማሪዎች ለሚያቀርባቸው አገልግሎቶች የሚመድበው በጀት ለታለመለት አላማ መዋሉን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል።


 

ቴክኖሎጂው የወረቀት አሰራርን በማስቀረት የሰው ኃይል ብክነትን ከመቀነስ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ያነገበ ነው ያሉት ደግሞ የአጼ ፋሲል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ኃይለገብርኤል አንዱአለም ናቸው።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ዑመር ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የተማሪዎችን ውጤትና ስነ ምግባር ለመከታታል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ቴክኖሎጂው የተማሪዎችን አጠቃላይ መረጃ አጣምሮ የያዘ በመሆኑ ለትምህርት ቤት ፣ለወላጆችና ተማሪዎች እፎይታን የሚሰጥ እንደሆነ  አብራርተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም