ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መስክ ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ ቀጥላለች

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 25 /2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መስክ ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ መቀጠሏን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ገለጹ።

አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በዓለም አቀፍ መድረክ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ዘርፍ ውስጥ የላቀ አስተዋጽዖ ስታበረክት የቆየች አገር መሆኗን አንስተዋል። 

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በግንባር ቀደም የመንግሥታቱ ማኅበር አባልና ቀጥሎም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት መሥራች አገራት መካከል አንዷ መሆኗንም ነው የገለጹት። 

ኢትዮጵያ በተለይም በአፍሪካ በቅኝ አገዛዝ ሥር ወድቀው ለቆዩት የአፍሪካ አገራት ጭምር ድምፅ በመሆን የረዥም ዘመን የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መስክ ውስጥ ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ የቆየች አገር መሆኗንም ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ መድረክ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ስታደርግ የቆየች አገር መሆኗን አንስተው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲዋን እያጠናከረች መምጣቷን አስረድተዋል።

በሰላምና ጸጥታው ዘርፍ ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ድርጅት እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሚመሩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በመሰማራት ያላት አስተዋጽዖ እጅግ ሰፊ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም በጎረቤት አገራት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አበርክቶ ማድረጓን ጠቅሰው፤ በቀጣናውም ሆነ በአፍሪካ ሰላም እንዲሰፍንና ልማትና እድገት እዲሳለጥ የምታበረክተውን አስተዋጽዖ  አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል። 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ  በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና እየተሰጠው መምጣቱን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የምታከናውነው የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የሚተከለውን ችግኝ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ግንዛቤ እንዳለው ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም