ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎዋ እስካሁን ስንት ሜዳሊያ አግኝታለች? 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎዋ እስካሁን ስንት ሜዳሊያ አግኝታለች? 

የ128 ዓመት ታሪክ ያለው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተጀመረው እ.አ.አ በ1896 በግሪክ አቴንስ ነበር። በወቅቱ 14 ሀገራት በታሪካዊው ስፖርታዊ ውድድር ላይ ተሳትፈዋል። 

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ የጀመረችው ውድድሩ ከተጀመረ ከ60 ዓመታት በኋላ ነው። 

ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ የተሳተፈችው በአውስትራሊያ ሜልቦርን እ.አ.አ በ1956 በተካሄደው 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነው።

ኢትዮጵያም በመጀመሪያ ተሳትፎዋ በአትሌቲክስና ብስክሌት 12 ስፖርተኞችን ይዛ ቀርባለች።

በመጀመሪያው የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ምንም ሜዳሊያ ባለመግኘቷ ደረጃ ውስጥ መግባት አልቻለችም። 


 

ኢትዮጵያ የዘንድሮውን የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ በውድድሩ ታሪክ ለ15ኛ ጊዜ ነው። 

ከዚህ ቀደም በነበራት የ14 ጊዜ ተሳትፎ በአትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ውኃ ዋናና ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርቶች ተሳትፋለች።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ የእስካሁኑ ተሳትፎዋ 23 የወርቅ፣ 12 የብር እና 23 የነሐስ በአጠቃላይ 58 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። ሁሉም ሜዳሊያዎች የተገኙት በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ነው። 

36 አትሌቶች 58ቱን ሜዳሊያዎች አስገኝተዋል።

ኢትዮጵያ በፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስና በውኃ ዋና 38 ስፖርተኞችን አሳትፋለች። 

የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም