በአማራ ክልል ዘላቂ ሠላምን በማስፈን የታቀዱ የልማት ተግባራትን ለማሳካት ክትትልና ድጋፉ ይጠናከራል- አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ዘላቂ ሠላምን በማስፈን  የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ለማሳካት ክትትልና ድጋፉ እንደሚጠናከር  የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።

አፈጉባኤዋ ምክር ቤቱ ያካሄደውን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ መጠናቀቁን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የክልሉን የልማት ዕቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲፈፀሙ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም በዋናነት የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑና ለኤክስፖርት የሚውሉ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ምክር ቤቱ አስፈፃሚውን አካል በመከታተል ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራን ከግብርናና ኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታትም እንዲሁ። 

ለህዝብ የገባነውን ቃል የምንፈፅመው ሠላምን በማስፈንና ልማቱን በማፋጠን የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጎ በመስራት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ በተገቢው መንገድ እንዲፈፀምም ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው በተሰጣቸው ኃላፊነት ልክ ተቀናጅተውና ተናበው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተለይ ሠላሙን አፅንቶ የህዝብ ተሳትፎን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት በስፋት መከናወን እንዳለባቸው አፈጉባኤዋ አመልክተዋል።

የምክር ቤት አባላትም መንግስት ለህዝቡ የገባቸውን ቃሎች ለመፈፀማቸው በልዩ ትኩረት የክትትልና ቁጥጥር ስራቸውን ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለአሰራር ከፍተት ያለባቸውን ህጎችና ደንቦችን ከማሻሻል ባለፈ የወጡ ህጎች ተፈፃሚ እንዲሆኑም የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

እንዲሁም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ለልማት ስራው እንዲውል ከማስገንዘብ ባለፈ የፀደቀው በጀት በቁጠባ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲውሉ የምክር ቤት አባላት ተገቢውን ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሠላሙን ለማፅናት  በየደረጃው ያለው ህብረተሰብ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት የድርሻውን እንዲወጣም አፈ ጉባኤዋ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ ምክር ቤት 8ኛው መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠት ዛሬ መጠናቀቁን ቀደም ሲል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም