የኃይማኖት ተቋማት የአብሮነት እሴትን በማጠናከር በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት መረባረብ ይጠበቅባቸዋል- ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት መከባበርና የአብሮነት እሴቱን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ጉዳዮችን በመከላከል በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መረባረብ እንዳለባቸው ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። 

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና የዕውቅና መድረክ "በጎ ለዋሉልን እናመስግን፤ ሰላማችንን እንጠብቅ" በሚል መሪ ኃሳብ ተካሂዷል።  


 

በመርኃ-ግብሩ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ የኃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል። 

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኃይማኖት መሪዎች በምዕመናን ባላቸው ተሰሚነት ምዕመናን በማስተማር በኩል የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም።  

በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በኃይማኖት መካከል የመከባበርና የአብሮነት እሴትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ተግባራትን መከላከል እንደሚገባ ገልፀዋል።  

ሰላም ከሌለ ልማትና እድገት ማምጣት እንደማይቻል ጠቅሰው፤  ሰላምን ለማፅናት የተባበረ ክንድ እንዲሁም  የኃይማኖት አስተምህሮና መንፈሳዊ ድጋፍ  ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።   

ይህንን ከግምት በማስገባት የኃይማኖት ተቋማት በአገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ እያከናወኑ ያለውን አዎንታዊ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው ፕሬዝዳንቷ የጠየቁት። 

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኃይማኖት ተቋማት አገርን በዘመናት ለማስቀጠል ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል። 


 

ኢትዮጵያውያን የአብሮነትና አንድነት እሴቶችን እንዲያዳብሩ የኃይማኖት ተቋማት ሚና ጉልህ እንደሆነም አንስተዋል። 

ሚኒስቴሩ የኃይማኖት ተቋማት ያላቸውን አቅም ለአገር ግንባታና ለዘላቂ ሰላም ለመጠቀም ከጉባዔው ጋር እያከናወነ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

የጉባዔው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፤ ጉባዔው በሰላምና መከባበር እሴት ግንባታ ላይ በትብብር ለመሥራት የተመሠረተ መንፈሳዊ ተቋም ነው ብለዋል። 


 

ይህንንም ተከትሎ በአገሪቱ ሕዝቦችና የኃይማኖት ተቋማት መካከል ለዘመናት የዘለቀውን የመከባበር፣ የመደጋገፍ ባህልን ለማጠናከርና ለትውልድ ለማስተላለፍ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለሰላም፣ መከባበርና አብሮነት እሴቶችን ማጎልበት የጀመረውን ጥረት ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አረጋግጠዋል።  

በመድረኩ የጉባዔው የ2016 በጀት ዓመት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ ለጉባዔው አስተዋጽዖ ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም