የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን ወደ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን ወደ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ በፌዴራል ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓትን ወደ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ገለጸ።
ባለሥልጣኑ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ተወያይቷል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ፤ በበጀት ዓመቱ የመንግሥት ግዥና አስተዳደር ሥርዓትን ዘመናዊ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልፀዋል።
በኦዲት ፍተሻ፣ የተገልጋይ እርካታን በማረጋገጥ፣ የተቋሙን አዳዲስ የአሠራር ሥርዓቶችን በማስተዋወቅና ቅንጅታዊ አሠራርን በማረጋገጥም መልካም ጅምሮች እንዳሉ አንስተዋል።
በዋናነት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን ከማጠናከር አኳያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በ169 ተቋማት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ አሠራር የኔትዎርክ መሠረተ-ልማት አቅርቦት አነስተኛ መሆንና በዘርፉ የሰው ኃብት አቅም ውስንነት የተስተዋለበት በመሆኑ አሠራሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት አብራርተዋል።
በመሆኑም መሠረተ-ልማቱን ካለማው ተቋም ጋር በመተባበር ይበልጥ የማዘመን ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ በቀጣይ ሁሉም ተቋማት በቴክኖሎጂው እንዲጠቀሙ ይደረጋል ብለዋል።
በባለሥልጣኑ የዕቅድና ስትራቴጂክ ዳይሬክተር ሉዋም አስፋው በፌዴራል ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውን ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ወደ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ለማስፋትም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ሙከራ ከተደረገባቸው መካከል አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች ተጠቃሽ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የተሽከርካሪ ሥምሪትና አስተዳደርን ማዘመን የሚያስችል የኢ-ፊሊት ማኔጀመንት ሶፍትዌር በማበልፀግ በተመረጡ 13 የፌዴራል ተቋማት ላይ በ2017 በጀት ዓመት የሙከራ ሥራ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ስለመጠናቀቁም አንስተዋል።
በቀጣይ በትኩረት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የተቋማት የግዥ ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሮኒክ ማድረግ፣ የተሽከርካሪዎች የነዳጅ ብክነት መቀነስ፣ አዳዲስ የአሠራር ማሻሻያዎችን ፈጥኖ ተግባራዊ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።