የመዲናዋን ፅዳት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን በተሰራው ስራ ህብረተሰቡን የፅዳቱ ባለቤት ማድረግ መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ የመዲናዋን ፅዳት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን በተሰራው ግንዛቤ የማሳደግ ተግባር ህብረተሰቡን የፅዳቱ ባለቤት ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፅዳት ኤጀንሲ  አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው በ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸምና በ 2017 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በዚሁ ወቅት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኤጀንሲው የከተማዋን ደረጃ የሚመጥን የፅዳት አጠባበቅ ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የተጀመረውን ተግባር የሚያሳልጡ የፅዳት ንቅናቄዎችን በማከናወን ውጤታማ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የመዲናዋን የፅዳት አጠባበቅ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ዘመናዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሳዲቅ ሽኩር በ2016 በጀት ዓመት ኤጂንሲው ያከናወናቸውን ዝርዝር ተግባራት የተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡


 

በዋናነት የመዲናዋን ፅዳት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን በተሰራው ግንዛቤ የማሳደግ ተግባር ህብረተሰቡን የፅዳቱ ባለቤት ማድረግ መቻሉን በሪፖርታቸው ገልጸዋል ፡፡

ህብረተሰቡ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ግንዛቤ እንዲኖረው 2 ሺህ ባለሙያዎች ተመድበው ብሎክን ማዕከል በማድረግ ቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኮሪደር ልማት የተገነቡ መንገዶችና ሌሎችም ዋና ዋና መንገዶች ፅዳት ለማስጠበቅ በየመንገዶቹ ዳር  988 ቆሻሻ መጣያዎች መገንባታቸውንም ገልጸዋል ፡፡

ደረቅ ቆሻሻ መሰብሰብና ጥቅም ላይ ማዋል አንዱ ስራ ዘርፍ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት ለ3 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡


 

የአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ ስድስት ጽዳት ኃላፊ ወይዘሮ ምስጋና በለጠ አዲስ አበባን ውብና ጽዱ ለማድረግ ኤጀንሲው የያዘውን ግብ ለማሳካት አበክረው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል ፡፡

የህብረተሰቡ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓት እየተቀየረ መምጣቱን ተከትሎ መዲናዋን ጽዱ የማድረግ ስራው ውጤት ማምጣቱን የገለጹት ደግሞ ከለሚ ኩራ ወረዳ የመጡት አቶ መገርሳ ጆቴ ናቸው ፡፡

በበጀት ዓመቱ 950 ሺህ 166 ቶን ደረቅ ቆሻሻ መሰብሰብ መቻሉና ከዚህም ውስጥ 90 ሺህ ቶን ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ መዋሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል ፡፡

ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ስራ ላይ የተሰማሩ ማህበራት በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ገቢ ማግኘታቸውም ተገልጿል ፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም