በኢትዮጵያ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ለቴክኖሎጂ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ለቴክኖሎጂ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ለቴክኖሎጂና ለሰው ኃይል ልማት ትኩረት መሰጠቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ያለማቸውን የንብረት፣ የሰው ኃይልና የፕሮጀክት አስተዳደር የዲጂታል ስርዓትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፥ ኢትዮጵያን ከልመና ለማላቀቅና የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ለግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
የአማራ ክልል በግብርናው መስክ ለሀገር ዕድገት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
በቱሪዝም ዘርፉም ከነባር ቅርሶች ባሻገር እንደጎርጎራ ያሉ ውብ መዳረሻዎች መገንባታቸው ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማዘመን ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ እንደሆነም አንስተዋል።
ከዚህ አኳያ የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የንብረት፣ የሰው ኃይልና የፕሮጀክት አስተዳደርን ለማዘመንና ስራን ውጤታማ ለማድረግ ያስጀመራቸው የአይሲቲ መሠረተ ልማቶች የሚያበረታቱ ናቸው ብለዋል።
የውሃ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በአግባቡና በግልፅ ለመምራት የተጀመረው የዲጂታል ስርዓት አበረታች ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የዲጂታል ዘርፉን በአግባቡ የሚመራና የሚያስፈጽም የሰው ኃይል ግንባታ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቱን ከዘመኑ ዕድገትና ለውጥ አኳያ በየጊዜው ማሻሻል አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የለሙ መሠረተ ልማቶችን ከዘራፊዎችና ከሳይበር ጥቃት መከላከል የግድ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ከሌሎች ተቋማት ጋር የተናበበ አገልግሎትን መዘርጋትም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቴክኖሎጂ አሰራርን ለማዘመንና አገልግሎትን ለማፋጠን ጉልህ ሚና እንዳለው በመግለጽ ይህንን በውጤታማነት ለመጠቀም ለሰው ኃይል ግንባታ ትኩረት መስጠት ይገባል ነው ያሉት።
የውሃና ኢነርጂ ቢሮ በቴክኖሎጂ ለተደገፈ ዘመናዊ አሰራር ያሳየው ተነሳሽነት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፥ የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሰሶ የቴክኖሎጂ ልማት ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ያስጀመራቸው የዲጂታል አገልግሎቶች በተለይ የህዝብ የአገልግሎት እርካታን ለማሻሻል የጎላ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው በአግባቡ ውጤት እንዲያመጣ የሰው ኃይል ሙያዊነት እውቀትና ስነምግባር ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
መሰል የዲጂታል አገልግሎት ፕሮጀክቶችን በዘላቂነት ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የዲጂታል አገልግሎቱ የህዝብን ቅሬታ የፈታ መሆኑን በየጊዜው መፈተሽ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
በ2017 በሁሉም ዘርፎች ዲጂታላይዜሽንን ለመተግበር መስራት እንደሚገባም አንስተዋል።