በፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ሜዳሊያ የምትጠብቅበት የ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ዛሬ ማምሻውን ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦በ33ኛው የፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ የሚካሄደው የ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል።

በፍጻሜው የሚካፈሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች በ32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት ሀገራቸውን ወክለው መወዳደራቸው ከዘንድሮው ተሳትፏቸው የተለየ ግጥምጥሞሽን ፈጥሯል።  

በፓሪስ እየተካሄደ የሚገኘው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ 8ኛ ቀኑ ላይ ይዟል።

በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ20 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም ይከናወናል። 

ኢትዮጵያ በፍጻሜው በሰለሞን ባረጋ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻና በሪሁ አረጋዊ ትወከላለች።

አትሌት ሰለሞን እ.አ.አ በ2020 በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

ለሁለተኛ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚሳተፈው አትሌት ሰለሞን 26 ደቂቃ ከ34 ሴኮንድ ከ93 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።

የመምና የጎዳና ላይ ውድድር ሯጭ የሆነው ዮሚፍ ቀጄልቻ በኦሊምፒክ ሁለተኛ ተሳትፎውን ያደርጋል። 


 

በቶኪዮ በተከናወነው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር ፍጻሜ 8ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

አትሌት ዮሚፍ እ.አ.አ ሰኔ 14 2024 በስፔን ማላጋ በተካሄደ የ10 ሺህ ሜትር ውድድር 26 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ ከ01 ማይክሮ ሴኮንድ በማስመዝገብ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።

ሌላኛው በውድድሩ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው አትሌት በሪሁ አረጋዊ ነው፤በሪሁ በ32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር ተወዳድሮ 4ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።


 

አትሌቱ እ.አ.አ በ2022 በኔዘርላንድ ሄንግሎ በተካሄደ ውድድር 26 ደቂቃ 46 ሴኮንድ ከ13 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት ተመዝግቧል። 

ሶስቱ አትሌቶች እ.አ.አ በ2020 በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ኢትዮጵያን ወክለው ተወዳድረው ነበር፤ ዘንድሮውም በተመሳሳይ ርቀት መሳተፋቸው የተለየ አጋጣሚ ሆኗል።

በ26 ደቂቃ ከ11 ሴኮንድ ከ00 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው የ27 ዓመቱ ዩጋንዳዊ ጆሹዋ ቼፕቴጋይ ውድድሩን ያሸንፋሉ ተብሎ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ይገኝበታል። 

ቼፕቴጋይ በ32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር የብር፣ በ5000 የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል፤ አትሌቱ የ5000 ርቀት የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ጭምር ነው።

በውድድሩ ጠንካራ ፉክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። 

ከፍጻሜው ውድድር በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 6 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በ1500 ሜትር ወንዶች ማጣሪያ ሳሙኤል ተፈራ፣ ኤርሚያስ ግርማና አብዲሳ ፈይሳ ይወዳደራሉ።

አትሌቶቹ በሚወዳደሩባቸው ምድቦች ከአንድ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ካጠናቀቁ እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ያልፋሉ።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች እየተገበረ ባለው  አዲስ አሰራር አትሌቶቹ ውድድራቸውን አጠናቀው ወደ ቀጣዩ ዙር ባያልፉ እንኳን በድጋሚ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባት በሚያስችላቸው የዙር ውድድር (repechage round) ይካተታሉ።

“ሬፔቼጅ ራውንድ” መሰናክልን ጨምሮ ከ200 እስከ 1500 ሜትር ርቀቶች አትሌቶች ወደ ቀጣዩ ዙር ባያልፉም ውድድራቸውን ካጠናቀቁ በድጋሚ የማለፍ እድል የሚያገኙበት የውድድር አማራጭ ነው። 

ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በ5000 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ ጉዳፍ ፀጋይ፣ መዲና ኢሳና እጅጋየሁ ታዬ ይሳተፋሉ።

አትሌቶቹ ከየምድባቸው ከ1 እስከ 8 ያለውን ደረጃ ይዘው ካጠናቀቁ ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።

ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ45 በ800 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ ፅጌ ዱጉማ፣ ሀብታም ዓለሙና ወርቅነሽ መለሰ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

አትሌቶቹ በየምድባቸው ከአንድ እስከ ሶስት ከወጡ እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው ግማሽ ፍጻሜ ያልፋሉ።

 በቀጥታ ካላለፉም በ “ሬፔቼጅ ራውንድ” የድጋሚ ማለፊያ የውድድር አማራጭ ውስጥ ይገባሉ።

በተያያዘም ትናንት በ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የእርምጃ ውድድር ፍጻሜ አትሌት ምስጋና ዋቁማ 6ኛ በመውጣት መልካምና ተስፋ ሰጪ ውጤት አስመዝግቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም