የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የአዲስ አበባ ስታዲየም የእድሳት ስራን ተመለከቱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳትና በዙሪያው ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እንቅስቃሴን ተመልክተዋል። 

ስታዲየሙ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) እና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የተቀመጡ መስፈርቶችን ባለማሟላቱ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ መታገዱ ይታወቃል።

ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ፊፋና ካፍ ባስቀመጡት መስፈርት መሰረት በስታዲየሙ እየተከናወኑ የሚገኙ የጥገና ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። 


 

የግንባታው ተቋራጮች ለሚኒስትሯ የስታዲየሙ እድሳት ያለበትን ደረጃና ተጓዳኝ ሁኔታዎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል። 

የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም መጀመሩን ኢዜአ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም የእድሳት ስራ በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ ዕድሳት ስራ  ተጠናቋል። 

የምዕራፍ ሁለት እድሳት ከ97 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ቀሪ ውስን ስራዎች በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ለስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ እድሳት 47 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለሁለተኛው ምዕራፍ 190 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።


 

ከስታዲየሙ ውጪ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የበይነ መረብ የቲኬት ሽያጭና በቴክኖሎጂ የታገዘ የደህንነት ስርዓት መዘርጋትን ጨምሮ ሌሎች በስታዲየሙና ዙሪያ ያሉ የውጫዊ ገጽታ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ከቀናት በፊት የብሔራዊ ስታዲየም (አደይ አበባ ስታዲየም) የግንባታ ሂደት በመጎብኘት ግንባታው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ደረጃውን ጠብቆ እንዲሰራ አቅጣጫ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም