ዕዙ የአካባቢውን ሰላም የማስከበር ተግባርና የአባላቱን አቅም በስልጠና ማጎልበት በተቀናጀ መልኩ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

ጅማ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦  የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የአካባቢውን ሰላም የማስከበር ተግባሩን እየፈጸመ በተጓዳኝ የአባላቱን አቅም በስልጠና በማጎልበት የተቀናጀ ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ለሁለት ወራት ያሰለጠናቸውን የሰራዊቱ ስልታዊ አመራር አባላትን  አስመረቀ።

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጀር ጄኔራል አብዱሮ ከድር በምረቃው ላይ እንደገለጹት፤ ዕዙ ከሌሎች ዕዞች ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም እያስከበረ ነው።

በአንድ በኩል የአካባቢውን ሰላም የማስከበር ተግባሩን እየፈጸመ በተጓዳኝ የአባላቱን አቅም በስልጠና በማጎልበት የተቀናጀ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ግዳጅ የመፈጸም አቅማችንን የማሳደግ ስራ የአባላትና አመራሩን አቅም ግንባታ የሚፈልግ በመሆኑ ለአቅም ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት።

ሲሰጥ የቆየው ስልጠናም ሰራዊቱ በአካል ብቃት እና በስነ-ልቦና ዳብሮ ለሀገሩ ክብር እና ሰላም አስተማማኝ መከታ መሆን የሚችል ስራዊት ለመገንባት እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ዕዙ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ ውጤታማ የህግ ማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ባለፋት ሁለት ወራት ሰልጥነው የተመረቁ አመራር አባላት በበኩላቸው በስልጠናው የደፈጣ እና መደበኛ ውጊያ ታክቲክና ስልትን ያጠቃለለ እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ሻለቃ ባያሌው ጥሩነህ፣ ስልጠናው ችግሮችን ቀድሞ በመረዳት የመቆጣጠር ስልት ላይ ተጨማሪ እውቀት ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

በስልጠናው በመደበኛና በደፈጣ ውጊያ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ታክቲኮችን ሰልጥነን የምንመራቸውን አባላት በዚሁ መሰረት ለማሰማራት ዝግጁ ነን ብለዋል።

መቶ አለቃ ዮናስ ብርቁ በበኩላቸው ስልጠናው አጠቃላይ ወታደራዊ ዝግጁነትን ያቀፈ ሲሆን፤ የመሪነት ሚናን የሚያጎለብት እውቀት የቀሰሙበት እንደሆነም አመልክተዋል።

በየትኛውም ዓይነት የውጊያ ስልት የአመራር ሚናና ሀላፊነት እስከምን ድረስ እንደሆነ የተማርንበት ብሎም የውጊያ ስልቶችን የተረዳንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም