አትሌት ኤርሚያስ ግርማና አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትር ማጣሪያ በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦ አትሌት ኤርሚያስ ግርማና አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትር ማጣሪያ በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።

33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ 8ኛ ቀኑን ይዟል።  

ቀትር ላይ በ1500 ሜትር ወንዶች የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ውድድር ተደርጓል። 

በምድብ 2 የተወዳደረው አትሌት ኤርሚያስ ግርማ 3 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ ከ21 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል። 

በምድብ 3 የተወዳደረው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ 3 ደቂቃ ከ37 ሴኮንድ ከ34 ማይክሮ ሴኮንድ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል። 

በምድብ 1 የተወዳደረው አትሌት አብዲሳ ፈይሳ 14ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ይሁንና  አትሌት አብዲሳ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የሚያስችለውን ዳግም እድል አግኝቷል።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች እየተገበረ ባለው አዲስ አሰራር አትሌቶቹ ውድድራቸውን አጠናቀው ወደ ቀጣዩ ዙር ባያልፉ እንኳን በድጋሚ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባት በሚያስችላቸው የዙር ውድድር (repechage round) ይካተታሉ።

በዚሁ መሰረት በማጣሪያው ውድድራቸውን ያጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች ወደ “ሬፔቼጅ ራውንድ” በመግባት የሚወዳደሩ ሲሆን የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፋሉ።

በሶስት ምድብ በተካሄደው ማጣሪያ ከየምድቡ ከአንድ እስከ ስድስት የወጡ አትሌቶች በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል። 

“ሬፔቼጅ ራውንድ” ወይም ሁለተኛ እድል መሰናክልን ጨምሮ ከ200 እስከ 1500 ሜትር ርቀቶች አትሌቶች ወደ ቀጣዩ ዙር ባያልፉም ውድድራቸውን ካጠናቀቁ በድጋሚ የማለፍ እድል የሚያገኙበት የውድድር አማራጭ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም