የእናቶችን ችግር ያቀለለ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት

የእናቶችን ችግር ያቀለለ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምቹ የመኖሪያ እና አረንጓዴ አካባቢ የሚያካትተውን የክረምት በጎ ፈቃድ በአዋሬ አካባቢ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎ በአዲስ አበባ በተለያየ አካባቢዎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት እድሳትና ግንባታ መርሃ-ግብር እየተከናወነ ይገኛል።

በከተማውም በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መኖሪያ ቤታቸው የታደሰላቸውና ደጋፊ የሌላቸው አቅመ ደካማ እናቶች እንደሚሉት መርሃ ግብሩ  ችግራቸውን አቃሎ እፎይታ እየሰጣቸው መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

እማማ እቴነሽ ገብረስላሴ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ አሁን ላይ የ93 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው።

ከወጣትነታቸው እድሜ ጀምሮ እንጀራ በመጋገር፣ የድግስ ምግቦችን በማዘጋጀትና የተለያየ የጉልበት ስራዎችን  በመስራት ይተዳደሩ እንደነበር ያስታወሳሉ።

ከጎናቸው የሚረዳቸው ልጅ፣ የቅርብ ዘመድና ቤተሰብ አለመኖሩ ደግሞ ድህነትንና ህመምን በብቸኝነት መግፋት ከባድ ፈተና መሆኑን ያስረዳሉ።

በዋናነት ደግሞ ለዘመናት ያለምንም ጥገና ይኖሩበት የነበረው ጠባብ ቤት በእጅጉ ማርጀቱን ተከትሎ ሌላ የህይወት ውጣ ውረድ እንደሆነባቸውም ይገልጻሉ።

እማማ እቴነሽ እንደሚሉት''እርጅናውም ሲጫነኝ ወጥቶ መስራቱ ሲቀር እንኳን ጣራና ግድግዳው የሚያፈስ ቤቴን ለማደስ በልቶ ማደርም ስቃይ ነበር'' ሲሉ የነበሩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያስታውሳሉ።

በተለይም ቤቱ ከመጸዳጃ ቤት ጋር ተያይዞ በመሰራቱ ችግሩን እንዳባባሰው ይገልጻሉ።

ይሁን እንጂ በበጎ ፍቃደኞችና መልካም ሰዎች ትብብር ቤታቸው ፈርሶ በአዲስ መልክ እንደተገነባላቸውና የዘመናት ችግራቸው እንደተቀረፈላቸው በደስታ ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት በአዲሱ ቤታቸው ቀሪ እድሜያቸውን ያለምንም ስጋት እየገፉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍና እገዛ በእጅጉ አመስግነዋል።

ሌላኛዋ የቤት እድሳት ተጠቃሚና የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሃያት አህመድና ወይዘሮ በሪሃ ደሊል ቀደም ሲል የነበረው ቤታቸው በእጅጉ ያረጀና ያዘመመ እንደነበር አስታውሰዋል። 


 

ወይዘሮ ሃያትና ወይዘሮ በሪሃ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ መሆናቸው ደግሞ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ ለአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ መዳረጋቸውን ይናገራሉ።

የገቢ ምንጫቸው ከቤተሰባቸው መሰረታዊ ፍጆታ የሚተርፍ ባለመሆኑ ቤቱን ማደስ የማይታሰብ እንደነበር ሁለቱም እናቶች ይገልጻሉ  ።

ይሁን እንጂ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት በጎ ፍቃደኞች ትብብር ቤታቸው በአዲስ መልክ በመታደሱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ይህ እድል የበጎ ፍቃደኞች ጥረትና ርብርብ ውጤት መሆኑን ጠቁመው፤ ሁሉም ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል።


 

የአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ኮሚሽን በበኩሉ በከተማዋ የሚሰጡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ረገድ አይነተኛ ሚና እያበረከቱ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብረሃም ታደሰ በበጎ ፍቃድ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የቤት ግንባታና እድሳት አንዱና ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ አገልግሎት ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ዜጎች፣ የአገር ባለውለታዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ የሚከናወን ነው።

በዚህ የቤት እድሳትና ግንባታ መርሐ-ግብር ያለ ምንም ክፍያ በጉልበታቸው የሚያገለግሉ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች፣ የግንባታ ባለሙያዎችና ባለሃብቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

በበጎ ፍቃድ የሚገነቡ ቤቶች ጽዱና ውብ አካባቢን በመፍጠር የነዋሪዎችን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ አስቸጋሪ በሆነ የኑሮ ሁኔታ የሚፈጠሩ ማህበራዊ ቀውሶችን ለማስቀረት አይነተኛ ሚና እንዳላቸው ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የዜጎችን የአኗኗር ዜዬ በመቀየር፣ የስራ እድልን በመፍጠርና ዘመናዊነትን በማላመድ ረገድ የበጎ ፍቃድ የቤት እድሳትና ግንባታ ፕሮግራም ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ በጎ ፍቃደኞች በተለያዩ መስኮች እየተሳተፉ ሲሆን 5 ቢሊየን ብር የሚገመት የልማት ስራ ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም