የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅብንን ድርሻ እየተወጣን ነው

አዳማ፤  ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፡- የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅብንን ድርሻ እየተወጣን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አመራር አባላትና ሰራተኞች ገለጹ።

በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤትና በ28 የግብይት ማዕከላት የሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ዛሬ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቻ ደምሴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የተሻለች ሀገር ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንዲሳካ ኮርፖሬሽኑ የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ ነው። 

በተለይ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ፣ የአፈር መከላትንና የአየር ብክለትን ለመከላከል፣ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ የሚቻለው በአረንጓዴ አሻራ ንቁ ተሳታፊ መሆን ሲቻል ነው ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማሳካት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ገዝቶ ወደ ተከላ መግባቱን ገልጸዋል።

በዚህም በዛሬው ዕለት በሁሉም የኮርፖሬሽኑ ማዕከላት ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ገመቺስ መላኩ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዓመታት ከ49 ሺህ በላይ ችግኞችን መትከሉን ጠቅሰው ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ከ31 ሺህ በላይ የሚሆኑት መፅደቃቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

ከፀደቁት ችግኞች መካከልም ቡና፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አቮካዶና ዘይቱንን ጨምሮ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች እንደሚገኙበትም ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት በ28ቱ የኮርፖሬሽኑ ማዕከላት ከ11 ሺህ 500 በላይ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በአዳማ  ማዕከል ብቻ 5ሺህ ችግኞች ተተክለዋል ብለዋል።

በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉ የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንዲሳካ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ችግኝ እየተከሉ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም በተከላው ረገድ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም