የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሠራተኞች በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል  አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

"የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ የሚገኘው 6ተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የተለያዩ ተቋማት የበኩላቸውን አሻራ እያሳረፉ ይገኛሉ።

ዛሬም የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሠራተኞች በተከታታይ አምስት ዓመታት አገር በቀል ችግኞችን ሲተክሉበት በነበረው በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ረሻድ ከማል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ ከቤት ልማት በተጨማሪ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የበኩሉን እያበረከተ ይገኛል።

ተቋሙ የቤት ልማት ሥራን ከአረንጓዴ ልማት ጋር አስተሳስሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በሌሎች ዓለማት በህንጻ ላይ ችግኝ የመትከል ተሞክሮን  በኮርፖሬሽኑ እንደሚተገበር ጠቁመዋል።

በኮርፖሬሽኑ ባለው ይዞታዎች የችግኝ ተከላ እያካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ የቤት ልማቱን ከአረንጓዴ አሻራ ጋር አስተሳስሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በአረንጓዴ ልማት ሥራው የአካባቢ ሚዛንን ከመጠበቅ ባለፈ ለመጪው ትውልድ የተሻለ አገር ለማስረከብ እንደሚያስችል ተናግረዋል። 

የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች የሆኑት ወይዘሮ አጸዱ ረጋሳ እና አቶ አማኑኤል አያሌው እንዳሉት ችግኝ በመትከል ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የበኩላችን እየተወጣን ነው ብለዋል።

ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን እንዲጸድቅ ስንከባከብ ቆይተናል ይህንን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም