የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የፋርማሲ ባለሙያዎች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦በሀገሪቱ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የፋርማሲ ባለሙያዎች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መድኀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር” የፋርማሲ ባለሙያዎች የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤን ከማጠናከር አንጻር ያላቸው ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ 44ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ ማካሄድ ጀምሯል።


 

በጉባዔው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መድኀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ማህበሩ የፋርማሲ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን የሚሰራቸው ስራዎች የሚበረታቱ እና ሊጠናከሩ የሚገቡ ናቸው ብለዋል።

የፋርማሲ ባለሙያዎች ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠርና የጤናው ዘርፍ አበረታች ለውጥ እንዲያመጣ ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የፋርማሲ ባለሙያዎች በሀገሪቱ ያለው መሰረታዊ የጤና አጠባበቅ ስርአት ውጤታማና ተደራሽ እንዲሆን ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር የህክምና ግብቶች ጥራታቸውንና ደህንነታቸውን ጠብቀው በበቂ ሁኔታና ጤናማ በሆነ መንገድ ለማህበረሰቡ እንዲደርሱ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በመንግስት የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የፋርማሲ ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፋቸውን ከምንጊዜውም በላይ  አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በሀገሪቱ ጤናማ የሆነ ማህበረሰብን ለመፍጠር ፋርማሲስቶች ሙያዊ ስነ ምግባርን የተላበሰ አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ሰይፉ በበኩላቸው ማህበሩ በሀገሪቱ የሚሰጡ የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ ይህንኑ ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል 44ኛውን ጉባኤ ምክንያት በማድረግ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ለሁለት ቀናት የሚቆይ ምክክር ማካሄድ መጀመሩን አስታውቀዋል ።

ጉባኤው መንግስት የጤና ተደራሽነት ለማረጋገጥ "ጤና ለሁሉም" በሚል መሪ ሃሳብ የሚሰራቸው ተግባራቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ከፋርማሲ ባለሙያዎች ምን ይጠበቃል የሚሉ ነጥቦችን በመለየት በዘርፉ የተሻለ ስራ ለመስራት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም