በጅማ ዞን  በመሬት መንሸራተት አደጋ  ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለማቋቋም ድጋፍ ይደረጋል

ጅማ፤ሀምሌ 26/2016 (ኢዜአ):- በጅማ ዞን  በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚደረግ የአደጋ ስጋት  አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) አስታወቁ።

የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጅማ ዞን በጎማ እና ጌራ ወረዳዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል።

የስራ ኃላፊዎቹ በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው የመሬት መንሸራተት አደጋ እየሰፋ ሄዶ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ለመከላከል ሰራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአደጋ ስጋት  አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ አሁንም አደጋው እየሰፋ እንዳይሄድ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ መሰራት አለበት።

ለዚህ ደግሞ ኮሚሽኑ ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመሆን የተጀመሩ የቅድመ መከላከል ስራዎች እንዲጠናከሩ አስፈላጊው ስራ ይሰራል ብለዋል።

በተለይም የአደጋው ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ከስጋት ቀጣና የማራቅ እና አደጋው የደረሰባቸውን ደግሞ መልሶ የማቋቋም እና የመደገፍ ስራ በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በመሬት መንሸራተቱ ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።


 

የጅማ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው የመሬት መንሸራተት አደጋው በዞኑ አልፎ አልፎ በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል።

የዞኑ አስተዳደርም በመሬት መንሸራተት አደጋው የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማዳበር ጭምር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ በጌራና ጎማ ወረዳዎች ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋም በርካታ ሰዎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉን አስታውሰዋል።

ምንም እንኳን የጉዳቱ መጠን የተለያየ ቢሆንም ችግሩ በዞኑ በሰባት ወረዳዎች መታየቱን የገለጹት አስተዳዳሪው በጌራ ወረዳ ብቻ 284 ነዋሪዎች ተጋላጭ ሲሆኑ 81 ቤቶች በአደጋው ፈርሰዋል ብለዋል።

አደጋው የደረሰባቸው ወገኖች በበኩላቸው ቤታቸው በመፍረሱ ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የጎማ ወረዳ ነዋሪ አቶ ገዛኸኝ ነጋሽ፣ የመሬት መንሸራተት አደጋው ቤታቸውን ያፈረሰባቸው በመሆኑ ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።


 

የደረሰባቸው ተፈጥሮአዊ አደጋ ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀላቸው በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።

በወረዳው የሊሙ ሻይ አካባቢ ነዋሪ አቶ በቀለ ደስታ በበኩላቸው ቤታቸው በናዳው ቢፈርስባቸውም የከተማው አስተዳደር የቤት መስሪያ ምትክ ቦታ የሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም አደጋው ሊስፋፋ ስለሚችል በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ቅደመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰቡት ነዋሪው ችግሩ በመንግስት በኩልም ትኩረት የሚፈልግ ነው ብለዋል።

በጉብኝቱ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) እና ሌሎችም የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም