በምስራቅ ጎጃም ዞን አንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን የቡና ችግኞች ይተከላሉ

ደብረ ማርቆስ ፤ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡-  በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው የክረምት ወቅት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን የቡና ችግኞች  ለመትከል ተ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 

የመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ተሾመ በላይ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ።

ለዘንድሮ ክረምት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን የቡና ችግኞች ተዘጋጅተው እስካሁን  472 ሺህ መተከላቸውን ተናግረዋል ።

ዘንድሮ አጠቃላይ በሚተከሉት ችግኞች ከ400 ሄክታር በላይ ተጨማሪ መሬት እንደሚለማ ጠቁመው ተከላው እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል ።

አርሶ አደሩ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በቡና ልማት በመሳተፍ ተጨማሪ ገቢ በማግኘት የኢኮኖሚ አቅሙን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በዞኑ እስካሁን 43 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና ተክል ተሸፍኗል።

በዞኑ የጎዛምን ወረዳ የጥጃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አንተናኔ አበበ እንዳሉት "በዚህ ክረምት በሩብ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ ተከላ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ልማቱን በማስፋፋት ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚተጉ አመላክተዋል።

"ከሰብል ልማት ስራቸው ጎን ለጎን በቡና ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የገራሞ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቢሻው ጌታቸው ናቸው።

ከዚህ በፊት በተከሉት ቡና በሚያገኙት ምርት ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ጠቅሰው በዚህ የክረምት ወቅትም ተከላ ለማከናወን የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም