ድርጅቱ በገዜ ጎፋ ወረዳ ለተቋቋሙ ጊዜያዊ የሕክምና መስጫ ማዕከላት ድጋፍ አደረገ

ጎፋ፤ ሀምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡- የአለም ጤና ድርጅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ለተቋቋሙ ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ማዕከላት የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ድጋፍ አደረገ።

ድርጅቱ ድጋፍ ያደረገው በገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የህክምና እርዳታ ለመስጠት ለተቋቋሙ ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ማዕከላት ነው።

ድጋፉ በወረዳው የተቋቋሙ አምስት ጊዜያዊ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ለማጠናከር እንደሚያግዝም በድርጅቱ የሀዋሳ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር በረከት ያለው ገልጸዋል። 

ድጋፉ በጠቅላላው 50 ሺህ ዶላር የሚገመት እገዛ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፣ በድጋፉ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመጠለያ ድንኳኖች ተካተዋል ብለዋል። 

በተጨማሪም ለሥራው አጋዥ የሆኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች ለሁለት ወር በኮንትራት አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ መደረጉን ነው ያስረዱት። 

ድጋፉን የተረከቡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ተቋሙ ላደረገው ድጋፍ በዞኑ አስተዳደርና በተጎጂዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም