በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ
ጎፋ ሳውላ፤ ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ተደረገ።
በክልሉ የመሬት መንሸራተትና ናዳ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ከአደጋ ስጋት ነጻ ወደሆኑ አካባቢዎች ለማዘዋወር እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
ድጋፉን ዛሬ ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ናቸው።
ከድጋፉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለት ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ አደጋው የደረሰባቸውን ወገኖች ለማጽናናት መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ኅዘኑን መግለጹን ጠቁመው፣ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል።
ሚኒስቴሩ አሁን ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ተጎጂዎች መልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉን ያጠናክራል ብለዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ “የደረሰው አደጋ አስደንጋጭና ልብ የሚሰብር ነው'' ብለዋል ።
ሚኒስቴሩ በሥሩ ካሉት የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ድጋፉን ማሰባሰቡን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው ተሊላ በበኩላቸው አገልግሎቱ በደረሰው አደጋ ተጎጂዎችን ለማጽናናትና ድጋፍ ለማድረግ በሥፍራው መገኘቱን ነው የገለጹት።
ለተጎጂዎች መርጃ እንዲሆንም አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማበርከቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በአካባቢው ጉዳት የደረሰበትን የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ለመተካት አዲስ ትራንስፎርመር ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ተጎጂዎች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የጀመረውን ድጋፍ እንደሚያጠናክርም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መስከረም አበበ እንዳሉት በደረሰው ጉዳት የሊጉ አባላት የተሰማቸውን ኅዘን ገልጸው፣ ሊጉ በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ 100 ሺህ ብር ድጋፍ ማበርከቱን ተናግረዋል።
ሊጉ በቀጣይም ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በማመላከት።
ድጋፉን ከተቋማቱ የተረከቡት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ ናቸው።
ኢንጂነር አክሊሉ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ በክልሉ መንግሥት ስም አመስግነዋል።
በክልሉ የመሬት መንሸራተትና ናዳ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ከአደጋ ስጋት ነጻ ወደሆኑ አካባቢዎች ለማዘዋወር ከፌዴራል መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።