4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ የኢትዮጵያን ገፅታ በመገንባት የጎላ ድርሻ እንደነበረው ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የተካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ የኢትዮጵያን ገፅታ በመገንባትና ቱሪዝምን በማስተዋወቅ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልገውን የፋይናንስ አቅርቦት ለማፈላለግ ያለመ ውይይት የተደረገበት እንደነበር አስታውሰዋል።

በጉባኤው ከ40 በላይ የሚሆኑ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከአንድ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የማስተናገድ የዳበረ አቅም እንዳላት ያረጋገጠ ነበር ብለዋል፡፡

ከጉባኤው ባሻገር 12 የጎንዮሽ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው፣ በሰላም፣ በጸጥታና በልማት ላይ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያስረዳንበት መድረክ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ፣ ቱሪዝምና ገጽታ ግንባታ ዘርፍ ውጤት ያገኘችበት ጉባኤ  እንደነበርም ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ስምሪት የተሰጣቸው 24 አዳዲስ አምባሳደሮች የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፊት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

አዳዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ያዳበሩትን ልምድና እውቀት ተጠቅመው ለሀገራቸውም ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት መከበር በትጋት እንዲሰሩ ሀላፊነት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ አምባሳደሮች ልምዳቸውንና የወሰዱትን ስልጠና ተጠቅመው ዘመኑን የዋጀ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማሳሰባቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በሳምንታዊ መግለጫቸው ያነሱት ሌላው ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሥራ ስምምነት ባልፈጸመባቸው የኤዥያ ሀገራት በህገ- ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎችን ከሀገራት ጋር በመነጋገር እየመለሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይም ተታለው ወደ ታይላንድና ማይናማር የሄዱ ዜጎችን ጃፓንና ህንድ ባሉ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች አማካኝነት እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም የኢትዮጵያ መንግስት ከነዚህ ሀገራት ጋር ምንም አይነት የሥራ ስምሪት ውል አለመፈራረሙን ተረድቶ ከህገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ የልዑካን ቡድን ነገ አዲስ አበባ ይገባል ብለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም