ኮሚሽኑ በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረገ

ሳውላ፤ ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች 14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረገ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት በመድረሱ የተሰማቸውን ኅዘን ገልጸው፣ በአደጋው ለተጎዱ  ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል። 

ኮሚሽኑ ለተጎጂዎች የተላከ 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ይዞ ወደስፍራው መምጣቱንም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በቀጣይም በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ቀጣይ እንቅስቃሴ የድርሻውን እንደሚወጣ ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም