የመምህራን ቅጥር ባልተከናወነበት መደብ ክፍያ ሲፈፅሙና ሲቀበሉ የተገኙ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ

ሆሳዕና ፤ሀምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፦በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ የመምህራን ቅጥር ባልተፈጸመበት መደብ ክፍያ የፈጸሙ የወረዳው የፋይናንስ አመራርና ባለሙያዎች እንዲሁም ደመወዝ ሲቀበሉ የተገኙ ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸው ተገለጸ።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው በሀድያ ዞን በሻሸጎ ወረዳ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በተሳተፉ ሶስት የፋይናንስ ባለሙያዎችና ሁለት የጥቅም ተጋሪ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ነው።

የሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዳኛ ጥላሁን ዴታሞ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የፅኑ እስራትና ገንዘብ ውሳኔው የተላለፈው በሻሾጎ ወረዳ የመምህራን ቅጥር ባልተፈጸመበት መደብ በ19 መምህራን ስም ክፍያ ፈጽመው በተገኙ ሶስት የፋይናንስ አመራርና ባለሙያዎች ላይ ነው።

በተጨማሪም መምህራን ሳይሆኑና ሳይቀጠሩ በጥቅም ተጋሪነት በባንክ አካውንታቸው በየወሩ ደመወዝ ሲቀበሉ የነበሩና በቁጥጥር ስር የዋሉ ሁለት ግለሰቦችም ውሳኔው እንደተላለፈባቸው ገልጸዋል።

ቀሪዎቹ አድራሻቸው በውል ያለመታወቁን ጠቁመው፤ ግለሰቦቹ በተገኙበት ተይዘው የሚቀርቡና ውሳኔ የሚተላለፍባቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

የፍርድ ውሳኔ ከተሰጣቸው መካከል የወረዳው የፋይናንስ ጽህፈት ቤት ምክትል የነበረው ግለሰብ ኃላፊነቱን ወደጎን በማለት የህዝብና የመንግስት ሀብትን ለአደጋ በመዳረግ በተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል መሰረት ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቱን ጠቅሰዋል።

ግለሰቡ ተጠርጥሮ የተከሰሰበት ከባድ የሙስና ወንጀል መሆኑንና ለፖሊስ እጅ እንዳልሰጠም በክስ ጭብጡ ላይ መመላከቱን ገልጸዋል።

ወንጀሉ ከባድ ስለሆነ በሌለበት የ11 ዓመት ጽኑ እስራትና 10 ሺህ ብር እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፉንም አመልክተዋል።

እንዲሁም ፋይናንስ ክፍያ ኦፊሰርና ፔሮል አዘጋጅ የነበሩ ሁለት ባለሙያዎች ደግሞ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራትና የ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ዳኛ ጥላሁን ተናግረዋል።

መምህራን ሳይሆኑና ሳይቀጠሩ በጥቅም ተጋሪነት ሰንሰለት በመፍጠር በስማቸው በባንክ አካውንት በየወሩ የሚገባውን ገንዘብ ለዘጠኝ ወራት ሲቀበሉ ከነበሩት 19 ግለሰቦች እስከ አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ክሱን ለማስተባበል ባለመቻላቸው የሦስት ዓመት ጽኑ እስራትና ሦስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደተወሰነባቸው ገልጸዋል።

ቀሪዎቹ አድራሻቸው በውል የማይታወቅ መሆኑን የጠቀሱት ዳኛ ጥላሁን፤ በፖሊስ ተይዘው በቀረቡ ጊዜ የፍርድ ውሳኔ እንደሚሰጣቸውም አመልክተዋል።

በዚህም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም ከ5 እስከ 11 ወራት በተፈፀመ ያልተገባ ክፍያ ከ730 ሺህ 239 ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሃብት እንዲመዘበር መደረጉን ከቀረበው ክስ መረጋገጡን አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ የተፈጸመውን ወንጀል በሰውና በሰነድ ማስረጃ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ተከሳሾችም ማስተባበል ባለመቻላቸውንና ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ሰራተኛው በስራ ገበታው ላይ ስለመገኘቱ ሙሉ መረጃ ለማግኘት የሚያስችል አሰራርን በመዘርጋትና የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር መሰል ወንጀሎችን መከላከል እንደሚቻልም በምክረ ሃሳባቸው አመላክተዋል።

የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ላልተገባ ዓላማ እንዳይውል መከላከል ከሁሉም ይጠበቃልም ብለዋል።

 

 

 

 
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም