በአማራ ክልል የእናቶች ጡት ማጥባት ሳምንት እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የእናቶች ጡት ማጥባት ሳምንት እየተከበረ ነው
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ''ክፍተትን በመሙላት ሁሉንም እናቶች ጡት እንዲያጠቡ እናድርግ'' በሚል መሪ ሃሳብ የእናቶች ጡት ማጥባት ሳምንት እየተከበረ ነው።
የክልሉ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ ጤና አገልግሎትና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ወንድሜነህ ልየው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የእናቶች ጡት ማጥባት ሳምንት ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1/2016 ዓ.ም እየተከበረ ነው።
የዓለም የእናቶች ቀን እናቶች ጡትን በማጥባት የልጆቻቸውን ዘላቂ ጤናና የአካል ጥንካሬ እንዲያስጠብቁ መነቃቃትን በሚፈጥር አግባብ እየተከበረ መሆኑን አስታውቀዋል።
እናቶች እስከ ስድስት ወር ያሉ ህጻናትን ምንም ተጨማሪ ምግብ ሳያስፈልጋቸው በአግባቡ እንዲያጠቡ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
የእናት ጡት የተሟላ የምግብ ንጥረ ነገሮችን የያዘ መሆኑን አመልክተው፤ እናቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ በማጥባት ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችንና የአካል ጉዳትን ቀድመው እንዲከላከሉ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
በተለይም ዕድሜያቸው ከስድስት ወር በታች የሆኑ ህጻናት የእናታቸውን ጡት ብቻ በአግባቡ እንዲጠቡ በማድረግ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋ በመፍጠር ረገድ ድርሻው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።
የዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት በዓለም ለ32ኛ፣ በኢትየጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ እየተከበረ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።