በመንግስትና በተለያዩ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እያገኘን ነው- በጎፋ ዞን በመጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች - ኢዜአ አማርኛ
በመንግስትና በተለያዩ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እያገኘን ነው- በጎፋ ዞን በመጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች
ሳውላ ፤ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፦በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሳቢያ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁለንተናዊ ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን ተናገሩ።
በወረዳው ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በቅርቡ የደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን የሰጡት እነዚህ ተፈናቃዮች ከዕለት ደራሽ በተጨማሪ የጤናና የስነ ልቦና ድጋፍም እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል ወጣት ኢዮብ ባሌ በአደጋው ወላጅ አባቱን፣ ታላቅ እህቱን እንዲሁም የአጎቱን ልጅ በሞት እንደተነጠቀ ተናግሯል።
ቤተሰቦቹ በዕለቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖቻቸውን ለመታደግ በሄዱበት ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግሯል።
መንግስትና የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ጠቅሶ፣ "የምግብ፣ የአልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ቁሶችን በበቂ ሁኔታ እያገኘን ነው" ብሏል።
በአደጋው ሲደግፋቸው የነበረውን የመጀመሪያ ልጅ በሞት የተነጠቁት ወይዘሮ አየለች ሶምባ በበኩላቸው ማሳቸውም በመሬት መንሸራተት ተገምሶ መወሰዱን ተናግረዋል።
በአደጋው ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ቢገኙም የተለያዩ አካላት እያደረጉላቸው ባለው ድጋፍና እገዛ እየተጽናኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ነፃ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውንም አክለዋል።
ወይዘሮ አየለች እንዳሉት ከሰብአዊ ድጋፎች ባሻገር የሕክምና እርዳታን ለተጎጂዎች የሚሰጡ በርካታ የህክምና ባለሙያዎች በቅርበት እየረዷቸው ይገኛሉ።
በሜሪ ስቶፕስ ኢንተርናሺናል ኢትዮጵያ የደቡብ ቀጠና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አለምብርሀን አሰፋ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ በመጠለያ ጣቢያው አቅራቢያ የሕክምና ማዕከል በማቋቋም ነፃ የህክምናና የስነ ልቦና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለም በአደጋው ምክንያት ንብረታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያጡና ስጋት ካለባቸው ቦታዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በሦስት ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።
አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ለእነዚህ ወገኖች አስፈላጊው ሰብዓዊ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ እርዳታዎች እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ እንዳሉት፣ ለተጎጂዎች በተቀናጀ መንገድ ሁሉም አይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።
ከደረሰባቸው የሥነ-ልቦና ቀውስ ፈጥነው እንዲያገግሙም የስነ ልቦና ህክምና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፣ በዘላቂነት ከሥጋት ነፃ በሆኑ ሥፍራዎች ለማስፈርም የቦታ ልየታ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ህብረተሰቡን የማወያየት ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።