በ800 ሜትር ማጣሪያ አትሌት ወርቅነሽ መለሰና አትሌት ፅጌ ዱጉማ በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜ አለፉ

አዲሰ አበባ፤ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ):- በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ800 ሜትር ሴቶች የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ አትሌት ወርቅነሽ መለሰና አትሌት ፅጌ ዱጉማ በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።

አትሌት ሀብታም ዓለሙ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ(Repêchage Round) ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ነገ በድጋሚ ትወዳደራለች።

በምድብ 3 የተወዳደረችው አትሌት ወርቅነሽ መለሰ 1ደቂቃ ከ58 ሴኮንድ ከ7 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች። በርቀቱ የነበራትን የግል ምርጥ ሰዓትም አሻሽላለች።

በምድብ 5 የነበረችው አትሌት ፅጌ ዱጉማ 1 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ከ90 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ ደረጃን በመያዝ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።

በአንጻሩ በምድብ 1 ተደልድላ የነበረው አትሌት ሀብታም ዓለሙ 2 ደቂቃ ከ2 ሴኮንድ ከ19 ማይክሮ ሴኮንድ ሰባተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ይሁንና አትሌት ሀብታም የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እየተገበረ ባለው የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ እድል(Repêchage Round) ነገ በድጋሚ ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ትወዳደራለች።

ነገ ከቀኑ 6 ሰዓት ከ20 በሚካሄደው የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ አትሌት ሀብታም በምትደለደልበት ምድብ ከአንድ እስከ ሶስት ከወጣች ወደ ግማሽ ፍጻሜው ታልፋለች።

የ800 ሜትር ሴቶች የግማሽ ፍጻሜ ውድድር እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ላይ ይካሄዳል።

በስድስት ምድቦች በተካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከየምድቡ ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ አትሌቶች በቀጥታ ለፍጻሜው አልፈዋል።

ዛሬ ቀደም ብሎ በ5000 ሜትር ሴቶች በተካሄደው የማጣሪያ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣አትሌት እጅጋየሁ ታዬና አትሌት መዲና ኢሳ ለፍጻሜው አልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም