ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሜዳሊያዋን በአትሌት በሪሁ አረጋዊ አገኘች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በ10,000 ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት በሪሁ አረጋዊ ሁለተኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።

ዩጋንዳዊው አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጋይ የኦሊምፒክን ክብረ ወሰን በመስበር ውድድሩን አሸንፏል።

ማምሻውን በተካሄደው የፍጻሜ ፍልሚያ አትሌት በሪሁ 26 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ከ44 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥቷል።

አትሌቱ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ ከኋላ በመነሳት ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የሚደነቅ ነበር።

አትሌት በሪሁ ከአራት ዓመት በፊት በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት ተወዳድሮ 4ኛ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

በ32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቶ የነበረው ሰለሞን ባረጋ 26 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ ከ48 ማይክሮ ሴኮንድ 7ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ 26 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ ከ02 ማይክሮ ሴኮንድ 6ኛ ወጥቷል።

ውድድሩን ዩጋንዳዊው አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጋይ የግል አጨራረስ ብቃቱን በመጠቀም በ26 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ከ14 ማይክሮ ሴኮንድ የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን በመስበር የወርቅ ሜዳሊያውን ወስዷል። ቼፕቴጋይ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ነው።

አሜሪካዊው ግራንት ፊሸር በ26 ደቂቃ ከ43 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥሩ ሊባል የሚችል የቡድን ስራ ቢሰሩም በመጨረሻው ዙር በአጨራረስ ድክመትና የመጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ ወደፊት ተስፈንጥሮ ሊወጣ የቻለ አትሌት ባለመኖሩ ምክንያት የታሰበው የወርቅ ሜዳሊያ ሳይገኝ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም