አቶ አገኘሁ ተሻገር የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ሥራዎችን ለማስጀመር ቡታጅራ ገብተዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፦ የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ሥራዎችን ለማስጀመር ቡታጅራ ከተማ ገብተዋል።

አፈ-ጉባኤው በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በተጠሪ ተቋማት የሚሰሩ የአቅመ ደካሞችን ቤት ዕድሳትና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ያስጀምራሉ።

አፈ-ጉባኤው ቡታጅራ ከተማ ሲደርሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ አፈ-ጉባኤውን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

መርሐ-ግብሩን የምክር ቤቱና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የክብር እንግዶች በተገኙበት በይፋ እንደሚያስጀምሩም ተመላክቷል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን በክረምቱ ለመትከል የያዘው 24 ሚልዮን የችግኝ ተከላ እቅድ አካል የሆነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም ይካሔዳል።

ምክር ቤቱ የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች አድሶ የማስረከብ እና ሌሎች ሀገራዊ የበጎ አድራጎት መርሃ-ግብሮችን ላለፉት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማከናወኑን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) "የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም