ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የመካከለኛ ርቀት የማጣሪያ ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦በፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚካፈሉባቸው የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ይካሄዳሉ። 

ዘጠነኛ ቀኑን ባስቆጠረው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ከቀኑ 6 ሰዓት ከ20 ላይ በሚደረገው የ800 ሜትር ሴቶች የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ (Repechage Round) አትሌት ሀብታም ዓለሙ በድጋሚ ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ትወዳደራለች።

አትሌት ሀብታም ትናንት በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ 2 ደቂቃ ከ2 ሴኮንድ ከ19 ማይክሮ ሴኮንድ 7ኛ መውጣቷ ይታወቃል።

በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ በምድብ አራት የተደለደለች ሲሆን በምድቡ 8 አትሌቶች ይሳተፋሉ። 

የሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ውድድር በአራት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን ከየምድቡ አንደኛ የሚወጡ አትሌቶች በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ይገባሉ። 

ከቀጥታ አላፊዎቹ ውጪ ሁለት ፈጣን ሰዓት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ግማሽ ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ። 

1 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ ከ71 ማይክሮ ሴኮንድ የአትሌት ሀብታም የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓት ነው።

በ800 ሜትር ሴቶች የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ (Repechage Round) 31 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

ትናንት በ800 ሜትር ሴቶች በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ አትሌት ፅጌ ዱጉማ አትሌት ወርቅነሽ መሰለ ከየምድባቸው አንደኛ በመውጣት በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸው ይታወቃል።

በስድስት ምድብ ተከፍሎ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ከየምድቡ ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ አትሌቶች በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል።

የግማሽ ፍጻሜ ውድድሩ ነገ ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ላይ ይከናወናል።

ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ በሚደረገው በ1500 ሜትር ወንዶች የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ (Repechage Round) ደግሞ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ይወዳደራል።

አትሌት አብዲሳ ትናንት በ1500 ሜትር ማጣሪያ በምድብ 1 ተወዳድሮ በ3 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ ከ67 ማይክሮ ሴኮንድ 14ኛ ወጥቶ ውድድሩን ቢያጠናቅቅም ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ሁለተኛ እድል አግኝቷል። 

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ‘Repechage Round’  ወይም ሁለተኛ እድል የተሰኘ አዲስ አሰራር አስተዋውቋል።

በአዲሱ የውድድር መመሪያ መሰናክልን ጨምሮ ከ200 እስከ 1500 ሜትር ርቀቶች የሚሳተፉ አትሌቶች በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር ባያልፉም በድጋሚ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባት በሚያስችላቸው ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመካተት እድል ያገኛሉ።

ይህ ሁለተኛ እድል ውድድራቸውን ያቋረጡ፣ ከውድድር ውጪ የተደረጉና ውድድር ያላካሄዱ አትሌቶችን አይጨምርም።

በዚሁ መሰረት አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በ1500 ሜትር ወንዶች ማጣሪያ በምድብ 1 የተደለደለ ሲሆን ከአንድ እስከ ሶስት ከወጣ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያልፋል። 

አትሌት አብዲሳ 3 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ከ37 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።  

የሁለተኛው ዙር ማጣሪያው በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚደረግ ሲሆን 27 አትሌቶች ይሳተፋሉ።  

በ1500 ሜትር ወንዶች ትናንት በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ አትሌት ኤርሚያስ ግርማና አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸው ይታወቃል። 

በሶስት ምድብ በተካሄደው ማጣሪያ ከየምድቡ ከአንድ እስከ ስድስት የወጡ አትሌቶች በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜው ማለፋቸው ይታወቃል።

የወንዶች 1500 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ነገ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ ይደረጋል።

በተያያዘም ትናንት በ10000 ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት በሪሁ አረጋዊ ሁለተኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።

 ኢትዮጵያ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ያገኘችው የመጀመሪያ ሜዳሊያም ሆኗል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም