የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በቡታጅራ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት አስጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በቡታጅራ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት አስጀመሩ።

አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ሥራዎችን ለማስጀመር ቡታጅራ ከተማ ገብተዋል።

አፈ-ጉባኤው በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በተጠሪ ተቋማት የሚሰሩ የአቅመ ደካሞችን ቤት ዕድሳት ያስጀመሩ ሲሆን በቀጣይ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግና የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ይከናወናሉ።


 

አፈ-ጉባኤው ቡታጅራ ከተማ ሲደርሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ አፈ-ጉባኤውን ጨምሮ የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባዔ ወ/ሮ ዛህራ ኡመድ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

መርኃ ግብሩ የምክር ቤቱና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የክብር እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።


 

የምስራቅ ጉራጌ ዞን በክረምቱ ለመትከል የያዘው 24 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ እቅድ አካል የሆነው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ይከናወናል።

ምክር ቤቱ የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች አድሶ የማስረከብ እና ሌሎች ሀገራዊ የበጎ አድራጎት መርኃ ግብሮችን ላለፉት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም