ኢትዮጵያን በውሃ ዋና ስፖርት የምትወክለው ሊና አለማየሁ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የማጣሪያ ውድድሯን ዛሬ ታደርጋለች

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን በውሃ ዋና ስፖርት የምትወክለው ሊና አለማየሁ በ50 ሜትር ሴቶች የነጻ ቀዘፋ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የማጣሪያ ውድድሯን ዛሬ ታከናውናለች።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በውሃ ዋና ስፖርት ስትሳተፍ የዘንድሮው ለአራተኛ ጊዜ ነው።

ዛሬ 9ኛ ቀኑን ባስቆጠረው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ውጪ በምትሳተፍበት የውሃ ዋና የስፖርት ዓይነት የማጣሪያ ውድድር ይደረጋል።

ዋናተኛዋ ሊና አለማየሁ በ50 ሜትር ሴቶች የነጻ ቀዘፋ ውድድር ትሳተፋለች።

ውድድሩ ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ 30 ሺህ 680 ተመልካች በሚያስተናግደው  ‘París La Défense Arena’ ሁለገብ የቤት ውስጥ የስፖርት ውድድር ማዕከል ይከናወናል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የምትሳተፈው ሊና በማጣሪያው በምድብ 2 የምትገኝ ሲሆን በአጠቃላይ በምድቡ 8 ተወዳዳሪዎች ለግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ይፋለማሉ።

የ50 ሜትር ሴቶች የነጻ ቀዘፋ ውድድር ማጣሪያ በ10 ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን ከየምድቡ አንደኛ የሚወጡ ዋናተኞች ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፋሉ። በተጨማሪም ከምድቦቹ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ ተጨማሪ 6 አትሌቶች ወደ ቀጣዩ ዙር ይሸጋገራሉ።


 

ዋናተኛዋ ሊና ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከሚያስችሏት ሁለት እድሎች አንዱን ካሳካች በዕለቱ ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ39 ደቂቃ ለሚካሄደው የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ማለፏን ታረጋግጣለች።

ሊና ለግማሽ ፍጻሜው አልፋ ማምሻውን በሚደረገው ውድድር ከምድቧ 1ኛ ወይም ፈጣን ሰዓት ከሚያስመዘግቡ 8 ዋናተኞች አንዷ መሆን ከቻለች ነገ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 ላይ ለሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር አላፊ ትሆናለች። 

31 ሴኮንድ ከ87 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው። ምርጥ ሰዓቷን ያስመዘገበችው በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም በጋና በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በ50 ሜትር ሴቶች ነጻ ቀዘፋ ውድድር ነው። 

ዋናተኛዋ ሊና በ50 ሜትር ሴቶች ነጻ ቀዘፋ መወዳደር የጀመረችው እ.አ.አ በ2018 ነው። ዋናተኛዋ ከዚህ ቀደም የ100 ሜትር ሴቶች ነጻ ቀዘፋ፣ የ4 በ100 (4x100) ነጻ ቀዘፋ የዱላ ቅብብልና 50 ሜትር ቢራቢሮ በዓለም አቀፍና አህጉራዊ መድረክ ላይ ተሳትፋለች።  

ሊና በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት ከ20 ኪሎ ሜትር ወንዶች የእርምጃ ተወዳዳሪ ምስጋና ዋቁማ ጋር የኢትዮጵያን ባንዲራ መያዟ የሚታወስ ነው።

እ.አ.አ በ2016 በሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ራሔል ገብረስላሴ እና እ.አ.አ በ2012 በለንደን በተከናወነው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ያኔት ስዩም በ50 ሜትር ሴቶች የነጻ ቀዘፋ ውድድር ቢሳተፉም ከመጀመሪያው ዙር ማለፍ አልቻሉም። 

ኢትዮጵያ በውሃ ዋና ስፖርት በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ስትሳተፍ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።

የመጀመሪያ ተሳትፎዋ እ.አ.አ በ2012 በለንደን በተካሄደው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነበር።

በወቅቱ ሙሉዓለም ግርማ በ50 ሜትር ወንዶች ነጻ ቀዘፋ ውድድር እንዲሁም ያኔት ስዩም በ50 ሜትር ሴቶች ነጻ የቀዘፋ ውድድር ቢሳተፉም ከመጀመሪያው ዙር አላለፉም።

እ.አ.አ በ2016 በሪዮ ዴጂኔሮ በተካሄደው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ሮቤል ኪሮስ በ100 ሜትር ነጻ ቀዘፋ፣ ራሔል ገብረስላሴ በ50 ሜትር ሴቶች ነጻ የቀዘፋ ውድድር ቢካፈሉም ከመጀመሪያ ዙር መሻገር አልቻሉም።

በቶኪዮ እ.አ.አ በ2020 በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አብዱልማሊክ ቶፊክ በ50 ሜትር ወንዶች ነጻ ቀዘፋ ቢሳተፍም ወደ ቀጣዩ ዙር ሳይሸጋገር ቀርቷል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም