በምዕራብ ወለጋ ዞን በተያዘው ክረምት በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞች ተተክለዋል

ጊምቢ፤ ሀምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ወለጋ ዞን በተያዘው ክረምት በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡና በሽታን የሚቋቋሙ የቡና ችግኞች በስፋት መተከላቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽፈት ቤቱ የቡናና ሻይ ልማት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም መስፍን፣ የተተከሉ የቡና ችግኞች ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙና በአጠረ ጊዜ ምርት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

በዞኑ የቡና ችግኝ የሚተከለው ከግንቦት አጋማሽ እስከ ሀምሌ መጨረሻ መሆኑን ጠቅሰው በተያዘው ክረምትም የዞኑን ህዝብ በስፋት በማሳተፍ በርካታ የቡና ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የቡና ችግኞቹ በ65 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተተከሉ ሲሆን በቡና ችግኝ ተከላው ላይ ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳታፋቸውን ገልጸዋል።

የቡና ችግኞቹም በ3 ሺህ 426 የግልና መንግስት ችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።


 

ዘንድሮ የተተከሉ የቡና ችግኞች የዞኑን የቡና ተክል ሽፋን ወደ 620 ሺህ ሄክታር መሬት ከፍ የሚያደርገው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የላሎ አሳቢ ወረዳ አርሶ አደር ሀብቴ ጋሩማ፣ ዘንድሮ ከ2 ሺህ በላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች መትከላቸውን ተናግረዋል።

የቡና ችግኞቹ በምርምር የተረጋገጡና በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡ እንዲሁም በሽታን የሚቋቋሙ መሆኑን ከግብርና ባለሙያ ግንዛቤ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

የጊምቢ ወረዳ አርሶ አደር ታከለ ፍቅሩ በበኩላቸው ባላቸው ሩብ ሔክታር መሬት ላይ በባለሙያ ምክር በመታገዝ የቡና ችግኝ መትከላቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ በየዓመቱ አዳዲስ የቡና ችግኞችን የመትከል ልምድ እንዳላቸውም ነው የተናገሩት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም