ኢዜአ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር  የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈጻሚ  አቶ ነጋሲ አምባዬ ገለጹ።

የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሀይቅ ከተማ ተገኝተው በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የኢዜአ አመራሮችና ባለሙያዎችም በእንጦጦ ፓርክ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አስቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ ለተከታታይ አመታት ችግኞችን በመትከል የራሱን አሻራ እያኖረ መጥቷል። 

በተቋሙ የሚተከሉ ችግኞች ሙሉ በሙሉ የአፈር ለምነትን በአጭር ጊዜ የሚመልሱ እና አገር በቀል እንደሆኑም ገልጸዋል።

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በተገቢው መንገድ እንዲጸድቁ ለመንከባከብ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በቀጣይም ተቋሙ የችግኞችን የጽድቀት ምጣኔ ከፍ ለማድረግ ፕሮግራም አውጥቶ እንክብካቤ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በችግኝ ተከላው የተሳተፉ አመራሮችና ባለሙያዎች  በበኩላቸው ፤ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር "የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም