የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፅዳት ኤጀንሲ አና በስሩ ያሉ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፅዳት ኤጀንሲ አና በስሩ ያሉ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ።

"የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሔደ ባለው ስድስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተለያዩ ተቋማት አሻራቸውን እያሳረፉ ነው። 

በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፅዳት ኤጀንሲ እና በስሩ ያሉ ተቋማት አመራርና ሰራተኞች  በረጲ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በችግኝ ተከላው ላይ በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቆንጅት ደበላ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) እና ሌሎችም አመራሮች ተገኝተዋል። 

በዚሁ ወቅት ምክትል ስራ አስኪያጇ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ  የአረንጓዴ አሻራ መዲናዋን ውበት በማላበስ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ መዲናዋን ውብና ፅዱ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።

በመዲናዋ በአረንጓዴ አሻራና በኮሪደር ልማት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለመንከባከብ እና ለመጠበቅ የሚያስችል የህግ ማእቀፍ ተግባራዊ መደረጉን በማንሳት ይህም አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፅዳት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ችግኞችን በመትከል ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል ።

የሚተከሉት ችግኞች ከውበት ባሻገር ለምግብነትም የሚውሉ በመሆናቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳላቸውም ነው የገለጹት።


 

በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የልደታ ክፍለ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኃላፊ አቶ በፍቃዱ ኃይሌ የመዲናዋ ነዋሪ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በመሳተፍ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ችግኝ መትከል ምቹና ጽዱ መኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት መንገድ ፅዳት ባለሙያ ወይዘሮ እልፍነሽ ታደሰ ተናግረዋል ።

የተከሉትን ችግኞች ለመንከባከብም ዝግጁ መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ አብራርተዋል ። 

በዘንድሮ ክረምት እንደ ሀገር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም