በወላይታ ዞን ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት እንዳያደርስ ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው 

ሶዶ ፤ሐምሌ 27/2016  (ኢዜአ)፦ በወላይታ ዞን የክረምት ዝናብን ተከትሎ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት እንዳያደርስ ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ እንደገለጹት በዞኑ በክረምት ዝናብ ምክንያት ሊከሰት የሚችለው የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ቀድሞ ለመከላከል ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ለአደጋው ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የመለየት ሥራ አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም በዞኑ ካዎ ኮይሻ፣ ኪንዶ ዲዳዬ፣ ኦፋ፣ ቦሎሶ ሶሬ እና ቦሎሶ ቦምቤ ወረዳዎች ለመሬት ናዳ ተጋላጭ እንደሆኑ መለየታቸውን ገልጸዋል።

ድጉና ፈንጎ፣ ዳሞት ወይዴ፣ ሆብቻ፣ ሁምቦና እና አበላ አባያ ወረዳዎች ደግሞ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የክረምቱ ዝናብ እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ የአደጋ ስጋት በሆኑ አካባቢዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆኑ አካባቢዎች የማስፈር ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል።

ሥራውን በሃላፊነት የሚያስተባብር ግብረ ሃይል ተቋቁሟል ያሉት አቶ ዳዊት፣ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራው  ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስካሁንም ካዎ ኮይሻ እና ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳዎች ውስጥ ለመሬት ናዳ የተጋለጡ ነዋሪዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፈር ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በአበላ አባያ ወረዳ ከአንድ ሺህ በላይ አባውራዎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆነ ቦታ በማስፈር በቋሚነት የማቋቋም ሥራ መሠራቱንም አስታውሰዋል።

የአበላ አባያ ወረዳ ነዋሪ አቶ አባይነህ ባላ በበኩላቸው አካባቢያቸው ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ በየጊዜው በእርሻ ማሳቸውና በንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ እንደነበር አስታወሰዋል።

ዘንድሮ ችግሩን አስቀደሞ ለመከላከል ከአካባቢያቸው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር የውሃ መሄጃ ትቦዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ይህም ድንገተኛ የውሃ ሙላት ሊያደርስባቸው ከሚችለው ጉዳት ራሳቸውን ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸው  ተናግረዋል። 

አካባቢያቸው ለመሬት ናዳ አደጋ የተጋለጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ደስታ ደንጎ የተባሉ የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። 

ከዞን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት በተላኩ የአደጋ ቅድመ መከላከል ኮሚቴ አባላት ሙያዊ ድጋፍ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ የተፈጠረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እሳቸውን ጨምሮ ህብረተሰቡ ከጎርፍና ከመሬት መንሸራተት አደጋ ራሱን ለመጠበቅ በቅድመ መከላከል ሥራዎች በንቃት እንዲሳተፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም