ፌዴራል ፖሊስ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባለፉት ዓመታት በተሰማራባቸው የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ሲያደርገው የቆየውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የፌዴራል ፖሊስ አመራርና አባላት በሀገራችን እየተተገበረ ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመከተል ኮልፌ በሚገኘው የልዩ ፀረ ሽብር መምሪያ ግቢ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


 

በመርሃ-ግብሩ ላይ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንደገለጹት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባለፉት ዓመታት በተሰማራበት የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ችግኝ ተከላ ሲያካሂድ ቆይቷል።

አሁን ላይም ይሄንን ተግባሩን ይበልጥ በተጠናከረ መልኩ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።

ፖሊስ ከህዝብ የወጣ የህዝብ ልጅ ስለሆነ በተለያዩ ጊዜያት ከህብረተሰቡ ጎን በመሆን በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም አቅመ-ደካሞችን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀዋል።


 

የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዋና ዓላማም ሀገራችን የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ላይ አሻራችንን ማሳረፍ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተሰማራበት በሀገራችን በአራቱ ማዕዘናት ሰላምና ፀጥታን በማስከበርና ሀገራዊ ተልዕኮውን በመወጣት እያስመዘገበ ካለው አመርቂ ውጤት ባሻገር ሀገራችን የምትከተለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ላይም በስፋት በመሳተፍ የድርሻውን እያበረከተ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ በማሳደግ ለፍሬ እንዲበቁ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ መግለጻቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም