በክልሉ ሠላም  በዘላቂነት ተጠብቆ ልማቱ እንዲፋጠን ሚናቸውን እንደሚወጡ የምክር ቤት አባላት ገለጹ

ባህር ዳር ፤ሐምሌ 27/ 2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሠላምን በዘላቂነት በማስጠበቅ   ልማቱ እንዲፋጠን የክትትልና የድጋፍ ተግባራቸውን  እንደሚያጠናክሩ  የክልሉ  የምክር ቤት አባላት ገለጹ። 

ሠላም ለዘላቂ ልማትና እድገት  ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም የምክር ቤቱ አባላት አመልክተዋል።  

በምክር ቤቱ ከሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ምርጫ ክልል የተወከሉት አቶ ጋሻው አስማሜ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  በክልሉ ሠላምን ለማስፈን  ህዝቡ አካባቢውን በመጠበቅ የበኩሉን  አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ተከታታይ ውይይት እየተደረገ ነው።

ችግር ውስጥ የገቡ ወገኖች ተመልሰው ከመንግስት ጋር ተቀራርበው በመወያየት ለችግሩ እልባት ሊሰጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ተመራጭ የምክር ቤት አባላትም ህዝብን በማወያየት የክልሉ ሰላም እንዲፀናና የታቀዱ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ ለሠላም ዋጋ መክፈል አለብን ብለዋል።

የክልሉ ሠላም በዘላቂነት ተጠብቆ  ልማቱ እንዲፋጠን እኔም ለመረጠኝ ህዝብ የሰላምን ዋጋ አጥብቄ በማስረዳት የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

ከሰሜን ሸዋ ዞን ግሼራቤል ምርጫ ክልል በምክር ቤቱ የተወከሉት አቶ አበራ ፈንታው በበኩላቸው፤ ያለሠላም መንቀሳቀስም ሆነ ልማትን ማፋጠን እንደማይቻል ተናግረዋል።


 

ሠላም ሰፍኖ  ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  የምክር ቤት አባላት ሚና ከፍ ያለ እንደሆነ ጠቅሰው፤ እሳቸውም በተመረጡበት አካባቢ ሰላም እንዲመጣ የክትትልና ድጋፍ ተግባራቸውን በማጠናከር ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ሠላም ለዘላቂ ልማትና እድገት  ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ  ሁሉም ህብረተሰብ ለዘላቂ ሠላም እውን መሆን ሊሰራ እንደሚገባ አመለክተዋል።

ማንኛውም አካል ችግሩን በውይይት  ሊፈታ እንደሚገባ ጠቅሰው ፤ይህ እንዲሳካም ድጋፋቸውን ለማጠናከር  ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በክልሉ  ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን  " ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል" ያሉት ደግሞ ከደቡብ ወሎ ዞን ተንታ ወረዳ ምርጫ ክልል የተወከሉት አቶ አሰፋ ይመር ናቸው።


 

ከመረጠን ህዝብ ጋር በጋራ ሃሳቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ሁላችንም ለሠላም ትኩረት ሰጥተን በመስራት ልማቱን ልናፋጥን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ሠላም ተጠብቆ  ልማቱ እንዲፋጠን የክትትልና ድጋፍ ሥራቸውን አጠናክረው ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።።

በመጠፋፋት የምናገኘው ትርፍ አለመኖሩን በመገንዘብ በክልሉ ዘላቂ ሠላም እውን እንዲሆን  ሁላችንም ተቀራርበን ችግሮችን  በውይይት ልንፈታ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ችግር ውስጥ የገቡ ወገኖች የሠላም ካውንስል ያቀረባውን የሠላም አማራጭ በመቀበል ለተግባራዊነቱ መዘጋጀት እንዳለባቸው  የምክር ቤቱ አባላት አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ከሐምሌ 22 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ሲያካሄድ የቆየው 8ኛ መደበኛ ጉባኤ  በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከርና  ውሳኔዎችን በማሳለፍ ማጠናቀቁን በወቅቱ ተገልጿል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም