በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር  የተተከሉ ችግኞችን ለውጤት ለማብቃት ተግተን እንሰራለን- በደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች

ደሴ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ  ለውጤት ለማብቃት  ተግተው እንደሚሰሩ በዞኑ አስተያየታቸውን የሰጡ  አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

በዞኑ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር 33 ሺህ ሄክታር መሬት የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑ የግብርና መምሪያው አስታውቋል።

በዞኑ ደሴ ዙሪያ ወረዳ የ037 ቀበሌ አርሶ አደር ሰይድ ይመር እንዳሉት፤  መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር  የሰጠው ትኩረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።

ይህም ባለፉት ዓመታት በተተከሉ ችግኞች የደን ልማትን ከማጠናከር ባለፈ የመሬታቸው የአፈር ለምነት ተጠብቆ  የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

እርሳቸውም ቀደም ሲል ከተከሉት ችግኞች በየሦስት ዓመቱ በመሸጥ እስከ 300 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ የክረምት ወቅትም ችግኝ ተከላ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተከልኩትን ችግኝም በአግባቡ በመንከባከብ ለውጤት ለማብቃት እሰራለሁ ብለዋል።


 

ሌላው በዚሁ ወረዳ የ038 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ በሽር ፤ ቀደም ሲል ከተከሉት ችግኝ  ለአጠና የደረሰውን በመሸጥ  በየዓመቱ በአማካይ 25 ሺህ ብር እንደሚያገኙ አውስተዋል፡፡

ዘንድሮም ከ2 ሺህ በላይ አፕልና ሌሎችንም  ችግኞችን ለመትከል ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ ያለሙ አካባቢዎችን በበጋው ወራት በተፋሰስ በማልማት፣ በክረምት ደግሞ ችግኝ በመትከል ተጠቃሚ እየሆንን ነው ያሉት ደግሞ በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ የ01 ቀበሌ  አርሶ አደር አደም መሐመድ ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት የተከሉት የማንጎ፣ ብርቱካንና የፓፓያ ችግኞች እየሰጧቸው ካሉት ምርት ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ በመበረታታት ተጨማሪ ችግኝ እንዲተክሉ ያነሳሳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ከፍራፍሬ ሽያጭ ከ20 ሺህ ብር በላይ ማግኘታቸውን አስታውሰው፤በዘንድሮው ክረምትም  የፍራፍሬ ችግኝ በብዛት እየተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መረሀግብር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ ጭምር በማሳውና በሌሎችም የወል መሬቶች ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ለውጤት እያበቃ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ምርታማነት እንዲጨምር፣ የደን ልማት እንዲጠናከርና ለእንሰሳት መኖ በቀላሉ ማገኘት እንዲቻል ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው ክረምትም 33 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታወቀዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን  ባለፈው ዓመት ክረምት 30 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ  የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውም  ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም