የአረንጓዴ አሻራ አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከምናደርገው ትግል አንዱ ነው - አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከምናደርገው ትግል አንዱ ነው - አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከምናደርገው ትግል አንዱ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ በቡታጅራ ከተማ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና በተጠሪ ተቋማት የሚሰሩ የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት አስጀምረዋል።
በተጨማሪም 300 ለሚጠጉ ተማሪዎች ለ 2017 ዓ. ም የሚሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶችን አበርክተዋል።
አፈ-ጉባዔውና ሌሎች አመራሮች ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ አካባቢን ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ትግል አካል መሆኑን አስረድተዋል።
የተጀመሩ የአረንጓዴ አሻራን የማኖርና የመንከባከብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ገልጸው፤ የተጀመሩ የልማት እንዲሁም ሰላምን የማጽናት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
መንግሥት የገባውን ቃል በሙሉ ይተገብራል ያሉት አፈ-ጉባዔው፤ ለዚህም በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሉ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለማከናወን በመምጣቱ ምስጋና አቅርበዋል።
ክልሉ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
እንዲሁም የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ምርታማነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ሰላምን የማጽናት እና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማጎልበት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
"የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው 6ኛው አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው።