የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።
አመራሮቹና ሰራተኞቹ ዛሬ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አየር መንገድ ጀርባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ የአካባቢ ጥበቃን እንደ አንድ ማህበራዊ ሀላፊነት ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከችግኝ ተከላው በተጨማሪ ለአካባቢ ምቹ እና ተስማሚ የሆኑ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ በማዋል የራሱን አስተዋፅዖ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
አዳዲስ እና ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የበረራ አገልግሎት ላይ በማዋል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ በአየር መንገዶች በሚደረገው ርብርብ አካል በመሆን የካርበን ልቀትን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንሰውን ዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ በመጠቀም እንዲሁም ቁሳቁሶችን መልሶ በመጠቀም ለአካባቢ ደህንነት መጠበቅ የራሱን ጉልህ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
40 ሄክታር በሚሆን ስፍራ ላይ 16 አይነት ሀገር በቀል የሆኑ 50 ሺህ ችግኞች ለመትከል ዕቅድ መያዙንና እስካሁን 27 ሺህ ያህል ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።
የተቋሙ ሰራተኞች የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡና በቀጣይም የአረንጓዴ አሻራ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።