የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትውልድ የመገንባት ሚናን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው - አቶ መሀመድ እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትውልድ የመገንባት ሚናን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው - አቶ መሀመድ እድሪስ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ታሪክ፣ እድገትና ትውልድ የመቅረጽ ጉልህ ሚና የነበረውና ይህን አጠናክሮ እየቀጠለ ያለ ተቋም መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
የልጆችን የንባብ ባህል ለማዳበር ከዲጂታል ዓለም በተጨማሪ በወረቀት፣ ብራናና በሌሎች የተጻፉ ጽሁፎችን እንዲያነቡ ማድረግ ይገባል ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የኢፕድ የቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ብላቴናት" የተሰኘ ልጆች ላይ የሚያተኩር ባለቀለም ሕትመት ያለውና ባለ 40 ገጽ መጽሔት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል።
በመጽሔት ምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ ሚኒስትሮች፣ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች፣ ደራሲያን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የእድሜውን ያህል አንጋፋና ጥበብ የተሸከመ የታሪክ ማኅደር የሆነ ተቋም ነው።
ተቋሙ ትውልድን የሚጠቅም ሀገር መገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተው፤ አሁን ላይ የጀመረው ሥራ ለሀገር የሚመጥን ትውልድ መገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ሌሎችም የተቋሙን አርዓያነት በመከተል ቀላል በሆነ መንገድ ለህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተለያዩ ሕትመቶችን ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ላለፉት ስምንት አሥርት ዓመታት ሀገርን ሲገነባና ትውልድ ሲያንጽ መቆየቱን አንስተዋል።
በ83 ዓመት ጉዞው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በየሳምንቱ በልጆች አምድ አስተማሪ ይዘቶች ሲያቀርብ እንደቆየ ተናግረው፤ ሀገር ተረካቢ ህፃናት የሕትመት ሚዲያ እንዲኖራቸው "ብላቴናት"ን ለማሳተም መብቃቱን ተናግረዋል።
መጽሔቱ በትምህርት ቤቶችና በሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት አማካኝነት የሚሰራጭ ሲሆን፤ በአዟሪዎች ማግኘት የሚቻል መሆኑንም ገልፀዋል።
መጽሔቱ ልጆች እየተዝናኑ እውቀት የሚገበዩበት፣ ስለሀገራቸው ወጥ አረዳድ እንዲኖራቸው፣ በስነ-ምግባር እንዲታነፁና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የይዘት ዝግጅቱ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች፣ የስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎችና ሰዓሊያን የሚሳተፉበትና በቀጣይ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የኢፕድ የቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከዲጂታል ዓለም በተጨማሪ ልጆችን በወረቀት፣ በብራናና በሌሎች የፅህፈት መሳሪያዎች የተፃፉ ጉዳዮችን እንዲያነቡ ማድረገ ይገባል ነው ያሉት።
የንባብ ባህልን ለማሳደግ ልጆች በሚውሉበት ስፍራ ፅሁፎችን ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነ አንስተው ለዚህም ከወላጆች ጀምሮ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
"ብላቴናት" በመላ ሀገሪቱ የሚሰራጭ፣ በቀጣይ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፤ አምዶችን በመከፋፈል ከ3 እስከ 9 ዓመት በላይ የሚሆኑ ልጆችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
"ብላቴናት" መጽሔትን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ መርቀውታል።