የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ

ሳውላ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚውል 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ መሀዲ(ዶ/ር) ምክር ቤቱ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ሀዘኑን ሲገልጽ እንደቆየ ገልጸዋል።

ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲውልም 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ስለሺ ኮሬ(ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው፤ በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ምክር ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ፤ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀዘኑን ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሰው፤ ለተደረገው ድጋፍም በተጎጂዎቹ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም