ባንኩ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን የባንኩ የሰው ሃይል ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ገለፁ።

የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር "የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ በመካሄድ ላይ ነው።

በዚሁ መርኃ ግብር የተለያዩ ተቋማት አሻራቸውን እያኖሩ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራርና ሠራተኞች በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።


 

የባንኩ የሰው ሃይል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እንዳሉት፤ ባንኩ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በተለያዩ ሀገራዊ መርኃ ግብሮች ላይ በንቃት እየተሳተፉ ይገኛል።

ከዚህም አንዱ በሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ንቅናቄ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባንኩ በዘንድሮው መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ማዕከል ብቻ ከ50 ሺህ በላይ ለምግብነት የሚውሉ፣ ሀገር በቀልና ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ዛፎችና ችግኞች ለመትከል አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከአዲስ አበባ ማዕከል በተጨማሪ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ 23 ዲስትሪክቶች የችግኝ ተከላው እንደሚካሄድ ነው የተናገሩት።

የባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለመጭው ትውልድ የተሻለች ሀገር የምናስረክብበት ነው ብለዋል።'


 

በዚህም ባንኩ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ በልዩ ትኩረት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርኃ ግብሩ የተሳተፉ ሰራተኞችም አሻራቸውን በማኖራቸው መደሰታቸውን ገልጸው ለእንክብካቤውም ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም