የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ለማስጀመር የቅድመ ምዝገባና ማረጋገጫ ሂደት ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ለማስጀመር የቅድመ ምዝገባና ማረጋገጫ ሂደት መጀመሩን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደችውን የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አለማቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማስቻል ያለመ ምክክር ከአለማቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተካሂዷል።

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የተመራ ልዑክ በካናዳ ሞንትሪያል ከአለማቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጁዋን ካርሎስ ሳላዛር ጋር በመገናኘት ምክክር አድርገዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ የዳበረ ልምድ ያላትና አለምን በአገልግሎት እያስተሳሰረ ያለ ግዙፍ የአየርመንገድ ባለቤት መሆኗን አስታውሰዋል።

አለማቀፉ የአቪዬሽን ድርጅት ከጉዞ ሰነድ የደህንነት ስራዎች ጋር በተያያዘ እያደረገ ላለው ድጋፍ ዋና ዳይሬክተሯ ምስጋና አቅርበዋል።

ድርጅቱ በቀጣይም ኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ስርዓት በምታደርገው የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠናን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፎች እንዲያደርግ ወይዘሮ ሰላማዊት ጠይቀዋል።

ዋና ዳይሬክተር ጁዋን ካርሎስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ስርዓት ለመግባት ያሳለፈችውን ውሳኔ በማድነቅ በቀጣይ ተቋማቸው የማይቋረጥ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ልዑኩ ከዚህ በተጨማሪ በየብስ የድንበር ቁጥጥር ላይ ተግባራዊ የሚደረገው ቴክኖሎጂ ከአለማቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ደረጃ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው የተቋሙ ሃላፊዎች ጋር ምክክር ተካሒዷል።

በቀጣይ ቀናትም ተመሳሳይ ምክክሮች እንደሚካሄዱ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም